
ጎንደር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማክሰኝት ከሚገኘው የምርምር ማዕከሉ የተገኙ የምርምር ውጤቶችን በተመለከተ እና ወባን መከላከል በሚቻልባቸው ሁኔታ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል፡፡ በመድረኩ በጎንደር ቀጣና የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች፣ የማኅበረሰብ ተወካዮች እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ የወባ ስርጭት ከባለፉት ዓመታት ቁጥሩ እንደጨመረ ገልጸዋል፡፡ የወባ ስርጭቱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እገዛ ማድረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ አንዱ ማሳያውም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አንዱ መኾኑን አቶ በላይ አብራርተዋል፡፡ መድረኩ እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ክልል እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ለመከላከል አቅጣጫ የሚቀመጥበት እና በቀጣይ በትኩረት ለመሥራት የሚያስችል መኾኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እንደሠራ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይም ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የወባ በሽታን ለመከላከል መንግሥት እና ባለድርሻ አካላት ከሚያደርጉት እገዛ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ለወባ መራቢያ የሚኾኑ አካባቢዎችን በማጽዳት እንዲሁም ለወባ መከላከል የሚቀርቡ ግብዓቶችን በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፡- ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!