“ባሕር ዳር ከተማ በተፈጥሮ የተዋበች፣ ለኑሮ የተመቸች፣ የጎብኚዎች ማዕከል የኾነች ከተማ ናት” ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር)

38

ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ለመሳተፍ ባሕር ዳር የገቡት ከፍተኛ መሪዎች የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር)፣ በሚኒስትር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መለሰ ዓለሙ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

መሪዎቹ በጣና ሐይቅ ዳርቻ እየተገነባ የሚገኘውን የጣና ማሪና እና በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ነው የተመለከቱት። በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) ባሕር ዳር ከተማ በተፈጥሮ የተዋበች፣ ለኑሮ የተመቸች፣ የጎብኚዎች ማዕከል የኾነች ከተማ ናት ብለዋል። ረጅሙን ወንዝ ዓባይን እና ጣና ሐይቅን የያዘችው ባሕር ዳር በብዙ ነገር የታደለች መኾኗን ገልፀዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ሰብዓዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ይህን ለማድረግ ደግሞ ጽዱ እና የተመቹ ከተሞችን የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በባሕር ዳር ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የሚበረታታ መኾኑንም ተናግረዋል። ለወትሮው ውብ የኾነችውን ከተማ ተጨማሪ ውበት የሚያላብሳት መኾኑን ነው የገለፁት።

በከተማዋ ያዩዋቸው የልማት ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠሩ መኾናቸውን አረጋግጠናል ነው ያሉት። ከተሞችን ማስዋብ የሚበረታታ መኾኑንም ተናግረዋል። በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በዋነኛነት የጎዳው የክልሉን ሕዝብ ነው ያሉት ኀላፊው የጸጥታ ችግሩ ሕዝቡ በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ፣ ሠርቶ እንዳይበላ ጎትቶታል ነው ያሉት። በክልሉ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ማስተጓጎል ክልሉ ወደ ኋላ እንዲቀር መፍረድ መኾኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ የመሠረተ ልማት ኢ-ፍትሐዊነት እንዲስተካከል የአማራ ክልል ሕዝብ መታገሉን ያስታወሱት ኀላፊው ታግሎ ባመጠው ለውጥ በርካታ መሠረተ ልማቶች መጀመራቸውንም ገልጸዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በክልሉ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ማስተጓጎሉንም ገልፀዋል። መጠናቀቅ የነበረባቸው ፕሮጀክቶች እንዳይጠናቀቁ አድርጓል ነው ያሉት።

ክልሉ የራሱን ሰላም ማረጋገጥ እና ልማቱን የሚያደናቅፉበትን ልክ አይደለም ብሎ መታገል አለበት ብለዋል። በክልሉ ያለውን የጸጥታ ችግር የበለጠ በማባዛት ኅበረተሰቡ ላይ ውዥንብር እንዲፈጠር ፕሮፓጋንዳ የሚሠሩ ኃይሎች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው ሰላም የለም የሚሉ ኃይሎችን እስከመጨረሻው ድረስ ታግሎ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም መገንባት ይገባል ብለዋል። በባሕር ዳር እየተገነቡ ያሉ የልማት ሥራዎች በክልሉ ከሰላም ማስከበር ሥራዎች ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችም እየተሠሩ መኾናቸውን ማሳያ ናቸው ብለዋል።

ያለው ተስፋ ሰጪ ጅምር የበለጠ እንዲሰፋ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በመተጋገዝ ሰላማችንን ማፅናት ይገባናል” የደብረ ማርቆስ ከተማ ወጣቶች፡፡
Next articleበባሕር ዳር ከተማ የተገነባው የገበያ ሸድ ለተጠቃሚዎች ተላለፈ፡፡