“የክልሉ እና የሀገር ብልጽግና እንዲረጋገጥ እየተሠራ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

22

ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ለመሳተፍ ባሕር ዳር የገቡት ከፍተኛ መሪዎች የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር)፣ በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መለሰ ዓለሙን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

መሪዎቹ በጣና ሐይቅ ዳርቻ እየተገነባ የሚገኘውን የጣና ማሪና እና በከተማው እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማቶችን ነው የተመለከቱት። ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ኢትዮጵያን በማዘመን ሂደት ውስጥ ከተሞችን የማስዋብ እና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። የጎበኟቸው የልማት ሥራዎች በመንግሥት ብቻ ሳይኾን በግል ባለሃብቶች የሚሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በትኩረት ከሚሠራባቸው ጉዳዮች መካከል ስብራቶችን መጠገን ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ይሄን ለመጠገን ባለሃብቶች ከመንግሥት ጋር በጥምረት እየሠሩ ነው ብለዋል። ፓርቲው ኢትዮጵያን ለማዘመን የባለሃብቶችን እና የመላ ሕዝቡን አቅም አቀናጅቶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የክልሉ እና የሀገር ብልጽግና እንዲረጋገጥ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ፓርቲው በብዙ ፈተናዎች ኾኖ ችግሮችን እንደ ድልድይ እየተጠቀመ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ነው ያመላከቱት። ፓርቲው የሕዝብን ችግር እየፈታ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

በችግር እየተደናቀፈ ሳይኾን ከችግር ላይ ትምህርት እየወሰደ ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል ነው ያሉት። የሀገር ሕልውና እና የሰላም ችግሮችን እየተሻገረ መምጣቱንም ተናግረዋል። ፓርቲው ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩትን ወደ አንድ አምጥቷል፤ አስታራቂ ሥራዎችን ሠርቷል ነው ያሉት። ሀገራዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ መሠራቱንም ገልጸዋል።

እንደ ሀገር ሰላም እና አንድነት እንዲረጋገጥ እየሠራ መኾኑን የተናገሩት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን አቅሞች መግለጡን ተናግረዋል። የኢትዮጵያን አቅሞች ማወቅ እና መግለጥ ኢትዮጵያን እንደሚያበለጽግ ነው የገለጹት። ፓርቲው እንደ ክልልም ኾነ እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል ነው ያሉት። የብዝኀ ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ መገኘቱን ነው የተናገሩት።

በግብርና እና በማዕድን ሃብት ላይ አዲስ ለውጥ እንዲመጣ መደረጉንም ገልጸዋል። ፓርቲው በጀመረው የሃሳብ ጥራት እና ልዕልና መሠረት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። የተረጋጋ ምጣኔ ሃብት እንዲኖር የተረጋጋ ሰላም ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉን ልማት ለማሳደግ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የሰላም ችግር ዕድገትን እንደሚጎትትም ተናግረዋል። የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንም ተናግረዋል። የሰላም እና የጸጥታ ችግሩን ለመፍታት ሕግ ከማስከበር ጎን ለጎን የሰላም አማራጮችን እየተጠቀሙ መኾናቸውን ገልጸዋል። የሰላም አማራጮች አሁንም ዝግ አይደሉም ብለዋል። ሰላማዊ አማራጮችን ተጠቅመው የሚመጡ ኀይሎችን ለመቀበል ዝግጁ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።

የክልሉ ሕዝብ መንግሥት እየሠራው ያለውን የሰላም ሥራ እንዲደግፍ፣ የታጠቁ ኀይሎች ሰላማዊ አማራጮችን እንዲጠቀሙ እና የራሱን ሰላም በራሱ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኮሪደር ልማቱ የባሕርዳርን ውበት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው” መለስ ዓለሙ
Next article“በመተጋገዝ ሰላማችንን ማፅናት ይገባናል” የደብረ ማርቆስ ከተማ ወጣቶች፡፡