
ደሴ: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማዋ የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ኢንስፔክተር አብዱ መሐመድ በኮምቦልቻ ከተማ ቦርከና ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ምርመራ ክፍል ኀላፊ ናቸው፤ በክፈለ ከተማው የስርቆት ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች ከነዘረፉት ንብረት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ከፍተኛ የሕዝብ እና የመንግሥት ሃብት የፈሰሰበት የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ተደጋጋሚ ስርቆት እየተፈጸመበት ይገኛል ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር አብዱ የስርቆት ወንጀል የፈጸሙትን የጸጥታ መዋቅሩ ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና የተዘረፈው ንብረትም በኤግዚቢትነት መያዙን አስረድተዋል፡፡
በክፍለ ከተማው በተቋማትም ሆነ በግለሰቦች ቤት ላይ የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የገለጹት የምርመራ ክፍል ኀላፊው በባቡር መሠረተ ልማቱ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ተደጋጋሚ ስርቆት ለማስቀረት ፕሮጀክቱን ሥራ ማስጀመር የተሻለው መፍትሔ ነው ብለዋል፡፡
የቢራሮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢንስፔክተር መሐመድ ይማም ከኦሮሞ ብሄረሰብ አሥተዳደር ደዋ ጨፋ ወረዳ ተሰርቀው ወደ ከተማዋ ገብተው የነበሩ ግምታዊ ዋጋቸው ከ1ሚሊዮን ብር በላይ የሚኾኑ የህክምና መሳሪያዎችን ከተጠርጣሪው ጋር በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ ጽሕፈት ቤታቸው የስርቆት ወንጀልን ለመከላከል ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ሥራ በመሥራቱ የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎችን መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዋና ክፍል ኀላፊ ኮማንደር ከድጃ አብዱ በከተማዋ የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡ በከተማዋ የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች የከተማዋን ሰላም ከማስከበር ባሻገር ወንጀሎችን በመከላከል ላይ በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙም ነው ኀላፊዋ የተናገሩት፡፡
በኅብረተሰቡ ጥቆማ መሠረት ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን መያዝ እንደተቻለ የገለጹት ኮማንደር ከድጃ የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ በርካታ ተጠርጣሪዎችን መያዝ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በምድር ባቡር መሠረተ ልማት ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶች አሳሳቢ መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡
በምድር ባቡር የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ ዝርፊያ ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ የተያዙ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ወንጀልን ለመከላከል ማኅበረሰቡ የምሽት ጥበቃ በማድረግም ጭምር ለጸጥታ ኃይሉ አጋዥ እየሆነ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!