
እንጅባራ: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በተለያዩ ከተሞች እና ወረዳዎች ሲከበር የቆየው 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ማጠቃለያ መርሐ ግብር በእንጅባራ ከተማ ተካሂዷል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙሉዓዳም እጅጉ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የቃል ኪዳናቸው ሰነድ የኾነው ሕገ መንግሥት የተፈረመበትን ቀን መነሻ በማድረግ በየዓመቱ ሕዳር 29 በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ተናግረዋል። የበዓሉ መከበር በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል የቆዩ የአብሮነት እሴቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማስቻሉንም አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል።
ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ብሔር ብሔረሰቦች በማንነታቸው ሳይሸማቀቁ ባሕላቸውን እና እሴቶቻቸውን ለሌሎች እንዲያስተዋውቁ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ኢትዮጵያ ብዝኀ ባሕል፣ ማንነት እና ቋንቋ ለዘመናት ተሰናስለው በጋራ የቆዩባት ሀገር መኾኗን አብራርተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት አተገባበር ላይ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊ የሚኾኑበትን ዕድል ፈጥሯልም ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው።
በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ለዘመናት ፀንተው የቆዩ የወንድማማችነት፣ የመከባበር እና በጋራ የመኖር እሴቶችን የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችን እና ተግባራትን በጋራ መታገል እንደሚገባም ዋና አሥተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
በበዓሉ ማጠቃለያም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሙዚቃ ዝግጅቶች፣ የባሕል አልባሳት እና የባሕል ምግቦች ትውውቅ ተካሂዷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!