
ደሴ: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የደሴ ከተማ ወጣቶች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የሰላም ውይይት አካሂደዋል። የደሴ ከተማ ወጣቶች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የአካባቢያቸውን እና የክልሉን ሰላም መጠበቅ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ነው የተወያዩት።
ክልሉ ከገጠመው የሰላም ችግር እንዲወጣ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል። በየአካባቢው ያላቸውን ተቀባይነት እና ተሰሚነት ተጠቅመው ሁሉም ለዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እንደሚሠሩ የውይይቱ ተሳታፊ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ ዓለማየሁ ሰላም ለሁሉም በእጅጉ አስፈላጊ መኾኑን ለመምከር መሠባሠባቸውን አስረድተዋል፡፡ የጸጥታ ኃይሉ በከፈለው መስዋዕትነት ደሴ ከተማ ሰላሟ ተረጋግጦ መቀጠሉን እና ከተማዋ ሰላም በመኾኗ ብዙ ማትረፏንም ጠቁመዋል።
ለከተማዋ ዘላቂ ሰላም የኅብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ አሸናፊ ልማት እንዲመጣ ከሚኖር ፍላጎት የበለጠ ለሰላም መስፈን በትጋት መሥራት ይገባልም ብለዋል። ሰላም ችግር ላይ በወደቀች ጊዜ ትውልድ ይባክናል፤ ሰላም ይሰፍን ዘንድ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለሚያደርጉት የሰላም ጥሪ ጆሮ መስጠት ብሎም ለመተግበር በትጋት መንቀሳቀስ ይገባል ነው ያሉት።
ሰላም ሲታጣ የወጣቱን የሕይዎት ማኅደር ያዛባል፣ የሕይዎት መስዋዕትነት ያስከፍላል፣ ልማትንም ያደናቅፋል፣ ሀገርም ያፈርሳል ያሉት አቶ አሸናፊ ለሰላም መስፈን ወጣቱ ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የበለጠ በትኩረት እንዲሥራም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- አሊ ይመር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!