
ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የፀረ ፆታዊ ጥቃት የነጭ ሪቫን ቀን ዘመቻን አስመልክቶ ከተለያዩ አካላት ጋር በባሕር ዳር እየመከረ ነው። የአማራ ክልል የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የፀረ ፆታዊ ጥቃት የንቅናቄ ዘመቻን አስመልክቶ “የሴቷ ጥቃት የኔም ነው፤ ዝም አልልም” በሚል መሪ መልዕክት ከተለያዩ መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር ምክክር አድርጓል።
የምክክሩ ዋና ዓላማ ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በስፋት ለመሥራት እንደኾነ የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ገልጸዋል። ኀላፊዋ የዚህ ጥቃት ሰለባዎች ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን ዋነኞቹ መኾናቸውን ተናግረዋል። ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ መኾናቸውን ኀላፊዋ ተናግረዋል።
የነጭ ሪቫን ቀን ሲከበር ሁሉም በየቤቱ ልጆቹን፣ እህቶቹን፣ እናቶቹን እና የትዳር አጋሮቹን ለመጠበቅ ከፍተኛ ኀላፊነት ሊወስድ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡ ኀላፊው እንዳሉት ይህ ጉዳይ የአንድ ተቋም ሳይኾን ሚዲያውም ኾነ ሌሎች ተቋማት የሴቶች እና ሕፃናት ጥቃት የሁሉም ጥቃት ነው በሚል ቁጭት ትኩረት ሰጥቶ ግንዛቤ በመፍጠር እና በመከላከል ጠንክሮ ሊሠራ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ነው የተናገሩት፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!