
ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት ማጠቃለያ መረሐ ግብር አካል የሆነ የፎቶ አወደ ርዕይ በአዲስ አበባ ከተማ ሳይንስ ሙዚዬም ተካሂዷል። በሳይንስ ሙዚዬም እየተከናወነ ባለዉ የፎቶ አዉደ ርዕይ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ መሪዎች እና አባላት የተሳተፉ ሲሆን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸዉ የከፈቱት ::
ባለፉት አምስት ዓመታት ፓርቲዉ በአጭር ጊዜ ሊጨበጡ እና በዉል የሚታዩ ሀገራዊ የልማት ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል። እነዚህን ተግባራት ለማስታወስ የፎቶ አወደ ርዕዩ አስረጅ መኾናቸውን ገልጸዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመስገን ጥሩነህ ፓርቲዉ ምስረታ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ የሚያኮሩ ተግባራትን ማከናወኑን አንስተዋል።
በዋናነት አካታች የፖለቲካ ሥርዓትን መገንባት፤ አረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ እና የሌማት ትሩፋት፤ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያስከብር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፤ ለዘመናት የቆዩ የኢትዮጵያ ስብራቶችን የሚጠግኑ ሥራዎችን ማከናዎን፤ ወደፊት አብሮ የማያስቀጥልን የተናጠል ትርክት ትቶ የወል ትርክት ማተኮር እና መሠል ተግባራት መከናዎናቸዉን አስታዉሰዋል።
የተሠሩት ሥራዎች በርካታ ቢሆኑም “ትልቅ ሕልም እንዳለዉ ሀገር ግን ገና ብዙ ይጠበቅብናል” ብለዋል። ሀገራችን ከፍተኛ ኢኮኖሚ ከሚኖራቸዉ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ትኾናለች፤ እንድትኾንም እንሠራለን ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆዬ ሲኾን የማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የፊታችን ቅዳሜ ኅዳር 21/2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!