የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር እየሠራ መኾኑን ገለጸ፡፡

21

ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር እና ሌሎች ተግባራትን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም እና ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል ወደ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሸጋገር የሚያስችለውን ዝግጅት እያከናወነ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚያስችለውን 13 የሚደርሱ መመሪያዎች እና ፖሊሲዎችን እያዘጋጀ ነው፡፡

ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወንም አንድ ዐቢይ እና 13 ንዑሳን ኮሚቴዎች በማቋቋም ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት፡፡ ስትራቴጂክ ፕላን በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው አካላት እና ለዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ መቅረቡንም ገልጸዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት የሽግግር ሂደት ልምድ እና ተሞክሮ መቀመር መቻሉን ጠቁመው ሂደቱ በጥሩ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የሽግግር ሂደቱን ለማገዝም የአሜሪካ እና የፈረንሳይ ኤምባሲዎች በዘርፉ ባለሙያዎች የታገዘ የሥልጠና እና የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ድጋፍ እየሰጡ እንደሚገኙም አመልክተዋል። ፕሬዚዳንቱ የዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ መብቶች የአካዳሚክ እና የአሥተዳደር ነጻነትን እንደሚያጎናጽፍም ጠቁመዋል፡፡

ሃብት የሥራ ዕድል እና ገቢን የሚፈጥሩ ዘጠኝ ተቋማት እና የሥራ ዘርፎች በጥናት መለየታቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡ በቅርቡም ሞዴል ፋርማሲ በመክፈት ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የመድኃኒት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ወደ ራስ ገዝነት ከሚሸጋገሩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መኾኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች በስፋት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በመደበኛው፣ በኤክስቴሽን እና በክረምት መርሐ ግብር ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
Next article“ትልቅ ሕልም እንዳለዉ ሀገር ገና ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል”ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ