
ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ሁሉም አካል የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ገልጿል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን በክልሉም ኾነ በሀገር ደረጃ በትርፍ አምራችነቱ ከሚታወቁ ዞኖች አንዱ ነው፡፡
ዞኑ በ2016/17 የምርት ዘመን ከ612ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን 23 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ይገኛል፡፡
በምርት ዘመኑ የታቀደው ዕቅድ እንዲሳካ ለማስቻል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ቢኾንም ለምርት ማሳደጊያ አገልግሎት የሚውል ከ1 ሚሊዮን 321ሺህ ኩንታል በላይ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ በምርት ዘመኑ ለአርሶ አደሩ ለምርት እና ምርታማነት ማሳደጊያ አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች በወቅቱ መቅረባቸው እና ክረምቱ ለሰብል የተመቸ የነበረ መኾኑ የቁም ሰብል ግምገማው የተሻለ መኾኑ መረጋገጡን ዞኑ ገልጿል፡፡
አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ኮምባይነሮችን እና ጉልበቱን በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን ለመሠብሠብ ባደረገው ጥረት እስካኹን ድረስ ከ244ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል መሠብሠብ ተችሏል ብሏል፡፡ ይሁን እንጅ ከኅዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ እየጣለ የሚገኘው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ስለመኾኑም ነው ዞኑ ያስገነዘበው፡፡
ሁሉም አካል የደረሱ የአቅመ ደካማ ሰብሎችን እንደ ደቦ እና መሰል አካባቢያዊ አደረጃጀቶችን እና ኮምባይነሮችን በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በመሠብሠብ፣ የተሠበሠበውን ደግሞ ደረቅ ቦታ ላይ በመከመር እና በሰዓቱ ወቅቶ ወደ ቤት በማስገባት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚገባ ዞኑ አሳስቧል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!