“በባሕር ዳር የሚሠራው የኮሪደር ልማት የከተማዋን የተፈጥሮ ውበት ይበልጥ እየገለጠ ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተሥፋዬ

63

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዎች እና አባላት 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ የባሕር ዳር ከተማን የኮሪደር ልማት የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል። በጉብኝቱ ላይ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተሥፋዬ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዎች እና አባላት ተገኝተዋል።

የምክር ቤት ዓባላቱ በከተማዋ የሚካሄደውን ልማት ከተመለከቱ በኃላ በግንባታው ላይ የሚሳተፉ ሠራተኞችን ምሳ በመጋበዝ አበረታተዋል፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በባሕር ዳር ከተማ የሚሠራው የኮሪደር ልማት በፍጥነት እየተከናወነ መኾኑን ስለመመልከታቸው ተናግረዋል።
በልማቱ ሥራ ላይ ከ700 በላይ ዜጎች በቀጥታ እየተሳተፉ መኾኑን ጠቅሰው የሠራተኞች ተነሳሽነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የዛሬው የምሳ ግብዣ ዋና ዓላማም በኮሪደር ልማቱ በመሳተፍ ባሕር ዳርን ለማስዋብ የሚተጉ ታታሪ ሠራተኞችን በሙሉ ለማመሥገን፣ ለማበረታታት እና ከጎናቸው እንደኾኑ ለማረጋገጥ መኾኑን ተናግረዋል። የኮሪደር ልማቱ ከውቡ ጣና ሐይቅ እና ከዘንባባዎች ጋር ተናብቦ የሚሠራ በመኾኑ የከተማዋን ተፈጥሯዊ ውበት የበለጠ የሚገልጥ እንደኾነም ዋና አፈ ጉባኤዋ አብራርተዋል።

በአማራ ክልል የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ባሕር ዳርን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች የሚሠሩ የኮሪደር እና ሌሎችም የልማት ሥራዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል። የኮሪደር ልማቱ በታቀደለት ጊዜ ውስጥ እና ጥራት እንዲከናወን ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ከዚህም በላይ ለማልማት አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን፣ ከአልባሌ ግጭት ወጥቶ ሙሉ አቅምን ለልማት ማዋል እና ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ በመቆም ኅብረ ብሔራዊ ሀገር መገንባት ያስፈልጋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የምክር ቤት አባላቱ የከተማዋን ልማት ተዘዋውረው በመመልከት ላሳዩት ትኩረት አመሥግነዋል።

ምልከታው እና የተደረገው ማበረታቻ መንግሥት ለልማቱ የሰጠውን ትኩረት፣ ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል የሚያመላክት ነው ብለዋል። በልማቱ ላይ ለሚሳተፉ ሠራተኞች እና ባለሙያዎችም ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል፣ በጊዜ አጠናቅቀን ለሕዝብ ለማስረከብም ያስችላል ነው ያሉት።

የኮሪደር ልማቱ አሁን ላይ በልዩ ትኩረት እየተገነባ ነው። የባሕር ዳር ልዩ ውበት መገለጫ የኾኑ ዘንባባዎች እና ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ዛፎችን ባከበረ መልኩ እየተከናወነ ስለመኾኑም አንስተዋል። የኮሪደር ልማቱ ሰው ተኮር እንዲኾን የሚያስችሉ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ተያይዘው እየተሠሩ ስለመኾኑም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

በኮሪደር ልማት ሥራው ላይ የሚሳተፉ ሠራተኞችም ልማቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሙሉ ጊዜ እና አቅማቸውን ተጠቅመው እየሠሩ ስለመኾኑ ገልጸዋል። የተፈጠረው ሰላም የሕዝብ ልማት እንዲሠራ፣ ራሳቸውም ተጠቃሚ እንዲኾኑ ስለማስቻሉም ተናግረዋል። የክልል ምክር ቤቱ ላደረገላቸው የማበረታቻ እና የአብሮነት መገለጫ የምሳ ግብዣም ምሥጋና አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም በዋጋ የማይተመን ሃብት መኾኑን በመረዳት የአካባቢያችንን ሰላም መጠበቅ ይገባናል” የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች
Next articleሕገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር እየሠራ መኾኑን የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡