“ሰላም በዋጋ የማይተመን ሃብት መኾኑን በመረዳት የአካባቢያችንን ሰላም መጠበቅ ይገባናል” የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች

38

ሰቆጣ: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰላም መደፍረስ ምክንያት ማኅበረሰቡ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ፣ ሠርቶ እና ነግዶ መኖር እየተሳነው ይገኛል። መንግሥትም ችግሩ በዘላቂነት ለመቅረፍ በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን በማቅረብ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁነቱን እየገለጸ ነው። በርካታ ታጣቂ ኃይሎች በሰላም ማኅበረሰቡን እየተቀላቀሉም ይገኛሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ ተቋማት፣ መሠረተ ልማቶች እና የከበረው የሰው ልጅ ሕይዎት ዋጋ ተከፍሎበታል። በጦርነት የሚገኝ ጀግንነትም ኾነ ጥቅም የለም ለታጠቁ ኃይሎችም ኾነ ለቤተሰቡ ቀውስን የሚያመጣ ነው ያሉት የሰቆጣ ወረዳ ነዋሪው አቶ አበባው መንግሥቴ ናቸው። በየወቅቱ በሚከሰቱ የዕርስ በርስ ጦርነቶች ምክንያት የኑሮ ውድነት መናር፣ አርሶ አደሩ አርሶ እንዳይበላ፣ ነጋዴው እንዳይነግድ ማድረጉንም አቶ አበባው ነግረውናል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ ደብሳ አየነው የሰላም እጦት መኖር እናቶች እንዲሳቀቁ እና የቁስ ብቻ ሳይኾን የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲያጋጥማቸው የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል። በሰሜኑ ጦርነት የወደመ ንብረት ሳይጠገን መሰል ጦርነት በክልሉ መከሰቱ የአማራ ክልልን ኢኮኖሚ ከድጡ ወደማጡ የሚወስድ መኾኑን አውስተዋል።

ከገጠመው ችግር ለመውጣት እናቶች ልጆቻቸውን ሊመክሩ እና ሊገስጹ ይገባል ነው የሚሉት ። ወጣቱ ከስሜታዊነት በመውጣት ነገሮችን በእርጋታ መመርመር ይገባቸዋል የሚለው ደግሞ ወጣት ብርሃኑ ሸጋው ነው። መረጃዎችን ከትክክለኛ ተቋማት በመከታተል ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ ነው የተናገረው። “ሰላም በዋጋ የሚይተመን ሃብት መኾኑን በመረዳት የአካባቢያችንን ሰላም ልንጠብቅ ይገባናል” ብለዋል ነዋሪዎቹ።

በሰቆጣ ወረዳ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ መንግሥት የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ እሚያምረው ጌጤ ተናግረዋል። የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ከወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ውይይቶች የተደረጉ መኾኑን የገለጹት አቶ እሚያምረው ጌጤ የወረዳው ሕዝብ ለሰላም ያለውን ቁርጠኛነት በተግባር አሳይቶናል ነው ያሉት።

በክልሉ ያለው የሰላም መደፍረስ ለክልሉ ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገርም የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ የሚል ኃይል ሁሉ ለክልሉ ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ችግሮቹን በውይይት ለመፍታት የሰላም መንገድን ሊከተሉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥራቱን የጠበቀ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ለመሥጠት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለስልጣን አስታወቀ።
Next article“በባሕር ዳር የሚሠራው የኮሪደር ልማት የከተማዋን የተፈጥሮ ውበት ይበልጥ እየገለጠ ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተሥፋዬ