ጥራቱን የጠበቀ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ለመሥጠት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለስልጣን አስታወቀ።

104

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለስልጣኑ በየደረጃው ከሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የ2017 ዓ.ም የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት አድርጓል።

የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዘውዱ ማለደ እንዳሉት ባለስልጣኑ በቴክኖሎጅ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ ይገኛል። በ2017 ዓ.ም የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ ጥራቱን የጠበቀ እና ተደራሽነቱን ያረጋገጠ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት መሥጠት፣ በቴክኖሎጅ የተደገፈ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ቁጥጥር ከተደረገባቸው 682 ሺህ 314 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 25 ሺህ 398 ጥፋተኛ ኾነው በመገኘታቸው 11 ሚሊዮን 921 ሺህ 180 ብር እንዲቀጡ ተደርጓል።
ቁጥጥር ከተደረገባቸው አሽከርካሪዎች 32 ሃሰተኛ መንጃ ፈቃድ እና ሰባት መንጃ ፈቃድ የሌላቸው መገኘታቸውንም ገልጸዋል።

በወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ለዘረፋ እና ያልተገባ ቀረጥ ወጭ መዳረግ፣ ኢ-ትኬቲንግ በተሟላ መንገድ አለመጀመር፣ ሃሰተኛ ማስረጃ፣ የመንገድ ደኅንነት እና መድን ፈንድ መዋቅር እንደ ክልል አለመፅደቅ እንደ ችግር ተነስቷል።

አሁን ላይ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩ በውይይቱ የተነሳ ሲኾን የአሽከርካሪዎች የተግባር ሥልጠና የጥራት ጉድለቱን እንዲሻሻል ማድረግ፣ ሃሰተኛ ማስረጃን ለመከላከል የማስልጠኛ ተቋማት በአዲሱ መስፈርት ፈቃዳቸውን ማደስ፣ ከሶፍት ዌር ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች ትኩረት መስጠት፤ የውስጥ እና የውጭ ቁጥጥር የቀጣይ ትኩረት መስኮች ኾነው ተቀምጠዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመንግሥት ትርጉም ባለው ዘላቂ ልማታዊ ሴፊቲኔት የዜጎችን ሕይዎት ለማሻሻል እና ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደኾነ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next article“ሰላም በዋጋ የማይተመን ሃብት መኾኑን በመረዳት የአካባቢያችንን ሰላም መጠበቅ ይገባናል” የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች