በአማራ ክልል በተካሄደው የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች ክትባቱን ወስደዋል።

28

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከኅዳር 9 እስከ 13/2017 ዓ.ም በተካሄደው የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት 82 በመቶ መፈፀሙን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የማኅጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ለታዳጊ ሴቶች መስጠት ከተጀመረ 6ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ባለሙያዎች ክትባቱ ከ90 በመቶ በላይ በሽታውን ለመከላከል ያስችላል ይላሉ።

በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚኾኑ የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር ታማሚዎች ሕመሙ ስር ከሰደደ በኋላ ወደ ጤና ተቋማት በመሄዳቸው በበሽታው ሕይዎታቸው የሚያልፍ ዜጎችን ቁጥር እንደ ጨመረው የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡ ክትባቱን አስቀድሞ መውሰድ በሽታውን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ መኾኑንም ነው መረጃው የሚያሳየው፡፡

ክትባቱ ባሳለፍነው ሳምንት ከኅዳር 9 እስከ 13/2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሰጥቷል፡፡ እንደ አማራ ክልልም በሁሉም ከተሞች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት ልጃገረዶች ሙሉ በሙሉ ክትባቱን ለማድረስ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በክልሉ 1 ሚሊዮን 501 ሽህ 644 አካባቢ ልጃገረዶችን ለማስከተብ በእቅድ ተይዞ 1 ሚሊየን 231 ሽህ 181 ልጃገረዶችን ማስከተብ እንደተቻለ የጤና ቢሮ የክትባት ኦፊሰር ተሰማ በሬ ተናግረዋል፡፡ ይህም ከእቅዱ 82 በመቶ የሚኾነውን ማከናወን እንደተቻለ ነው የገለጹት፡፡

ክትባቱ በ175 ወረዳዎች እንዲሰጥ ታስቦ በ171 ወረዳዎች መሰጠት ተችሏል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይተው ወደ ሥራ የገቡ እና ገና የሚጀምሩ ወረዳዎች ላይ ክትባቱ ሲሰጥ እቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡ ይህንንም ለማሳካት ከፍተኛ የኾነ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የማኅጸን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ በጣም አስከፊ እና ብዙ እናቶችን በየቤታቸው በሕመም እንዲሰቃዩ ብሎም ለሞት እንዲዳረጉ እያደረገ ያለ በሽታ በመኾኑ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የበሽታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ በአካባቢው ያልተከተቡ ልጃገረዶች እንዳይኖሩ እና እንዲከተቡ በማድረግ የበኩልን አስተዋጽኦ መወጣት ይኖርበታል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝብን በማሳተፍ እና በማስተባበር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤታማ እየኾነ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleመንግሥት ትርጉም ባለው ዘላቂ ልማታዊ ሴፊቲኔት የዜጎችን ሕይዎት ለማሻሻል እና ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደኾነ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡