
ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች የተሳተፉበት ወቅታዊ የሰላም እና የልማት ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ሕዝብ እና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እና በማስተባበር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤታማ ነው ብለዋል፡፡
በሰላም እና ልማት አጀንዳዎቻችን ላይ ከሕዝባችን ጋር እየመከርን በመሥራታችን ያመጣነውን አበረታች ለውጥ ለማስቀጠልም ቅንጅታችንን የበለጠ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
አመራሩ ኀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥልጠና መካሄዱ ተጨማሪ የመፈጸም አቅም የፈጠረ ከመኾኑ ባሻገር የተመዘገቡ ድሎች የሚያጠናክር እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡በፓርቲ እና በመንግሥት ሥራዎች የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶችን መጠበቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በቀጣይ የክልሉን ሰላም የማረጋገጥ ጉዳይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ የገለጹት ኀላፊው የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ እና በተለይም የልማት፣ የትምህርት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የፓርቲ እና የመንግሥት ተግባራትን አቀናጅቶ በመሥራት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በመግለጽ ከክልል ጀምሮ በየደረጃው ያለ አመራር እና መዋቅር ልዩ የድጋፍ እና ክትትልሥራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ እና ሌሎች የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አመራሮች እና የቢሮ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!