የተፈጠረው ቀውስ ወደ ሰላም ይመጣ ዘንድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

35

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው ቀውስ በማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ዓሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። በተለይ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚያስከትለው ችግር ከፍተኛ ነው። ይህን መሠረት አድርጎም በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በከተማው ከሚገኙ ሴቶች ጋር ስለ ሰላም የሚመክር የውይይት መድረክ ተካሂዷል

በመድረኩ የተገኘችው የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ ወጣት ብርቱካን ይሄነው በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ወላጅ አባቷን እዳጣች ገልጻለች፡፡ የቤተሰባቸው ሠብሣቢ የነበረውን ወላጅ አባታቸውን በማጣታቸውም ቤተሰባቸው ዘርፈ ብዙ ችግር እንዳጋጠማት ትናገራለች፡፡ ሰላም ለሁሉም መሠረት ነው የምትለው ወጣት ብርቱካን አሁን የተፈጠረው ቀውስ ወደ ሰላም ይመጣ ዘንድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ተናገራለች፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በከተማው ከሚገኙ ሴቶች ጋር ስለ ሰላም የሚመክረው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የከተማ አሥተዳሩ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃት ዘርፍ ኀላፊ ላቀች ሰማ በተፈጠረው የሰላም እጦት ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ የችግሩ ሰለባ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከመነጋገር እና ከመመካከር ባለፈ የተግባር ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል። የሰላም እጦቱ በሴቶች ላይ ዘርፈ ብዙ ችግር እያደረሰ መኾኑን የተናገሩት የውይይቱ ተሳታፊዎች ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሴቶች ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ፈንታነሽ አፈወርቅ የሰላም እጦቱ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ መኾኑን አስገንዝበዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ዘላቂ ሰላምን ከማምጣት ባለፈ ሴቶችን በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ዘላቂ ሰላም እንዲመጣም ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብሔር ብሔረሰቦች ቀን ባሕል እና ወግን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና አለው።
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማትን የሥራ እንቅስቃሴ እየተመለከቱ ነው።