
ባሕር ዳር:ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሦስት ዞኖች ማለትም በምዕራብ ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር እና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር እየተከናወነ ይገኛል። ትምህርት ቤቶቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁም 1ሺህ 400 ተማሪዎችን የማስተናገድ ዐቅም አላቸው። ይህም ለክልሉ ብቻ ሳይኾን ለሀገር የሚጠቅሙ ተወዳዳሪ እና ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት ያስችላል።
እንደነዚህ ያሉ ሥራዎችን ለማከናዎን ከግብር የሚሠበሠበው ገንዘብ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ ዘርፈ ብዙ የመልማት “ጥያቄዎችን መመለስ የሚቻለው በራስ ዐቅም ከሚሠበሠብ ገቢ መኾኑን” ተናግረዋል።
በከተማዋ ልዩ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ የግብር አሥተዳደር ሥርዓት ለመገንባት እና ገቢን ለማሳገድ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ኀላፊው ጠቁመዋል።
እንደ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በባሕር ዳር ከተማም በገቢ አሠባሠቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አቶ ኃለማርያም ጠቁመዋል። ይህም የሕዝቡን የመልማት ፍላጎት ወደ ኋላ ጎትቶታል ነው ያሉት። መምሪያው ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን የገቢ አሠባሠብ ተግባሩን አጠናክሮ መፈጸሙን ገልጸዋል።
የሕዝቡ ሰላም እና ደህንነት የሚጠበቀው እንዲኹም ዘርፈ ብዙ የመልማት ጥያቄዎችን መመለስ የሚቻለው በራስ አቅም ከሚሠበሠብ ገቢ እንጅ ከለጋሽ ሀገራት በሚገኝ ብድር አይደለም ያሉት ኀላፊው በ2017 ሩብ ዓመት ከ1 ቢሊዮን 682 ሺህ ብር በላይ መሠብሠብ ተችሏል ብለዋል። ይህም ከባለፈው ሩብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አሳይቷል።
በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ነጋዴዎች በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ አይደለም ያሉት ኀላፊው በቀጣይ የግብር ከፋዩን ማኀበረሰብ ግንዛቤ በማስፋት የተሻለ ገቢ ለመሠብሠብ ይሠራል ነው ያሉት። ግብር የመልካም አሥተዳደር ምንጭ እንዳይኾንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማሥተዳደር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።
ይህ ገንዘብ በአግባቡ ቢሠበሠብ እንደ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ኹሉ የተለያዩ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን ለማሳለጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
በአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት 71 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሠብሠብ መታቀዱን ከገቢዎች ቢሮ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!