
ደባርቅ: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ደባርቅ ከተማ አሥተዳደር የገጠር ቀበሌዎች በጣለው ከባድ በረዶ ምክንያት ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ በመውደሙ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን አርሶ አደሮች ተናግረዋል። ኅዳር 14/2017 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ ለ30 ደቂቃ የጣለው ከባድ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ በሶስት ቀበሌዎች ከ500 ሄክታር መሬት በላይ የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት አድርሷል።
ጉዳቱ በተለያዩ የሰብል አይነቶች ላይ የደረሰ ሲሆን ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍና ጥራጥሬ ሰብሎች ይገኙበታል። አርሶ አደሮቹም በአካባቢው ባሕል መሰረት ሰብላቸውን በደቦ ለመሰብሰብ ነገ ዛሬ በሚሉበት ወቅት ድንገት የጣለው በረዶ ሰብላቸውን ሙሉ በሙሉ እንዳወደመባቸው ተናግረዋል። አቶ ራራ ደሴ የተባሉ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ አርሶ አደር በደረሰው ጉዳት በማዘንና በመደናገጥ በርካታ አርሶ አደሮች ለከፋ የጤና ቀውስ መዳረጋቸውን አንስተዋል።
“ጉዳቱ ያልተጠበቀ ነው፤ እንኳን እኛ እንስሳቱ ራሱ የሚበሉት ድርቆሽ ሳር አልተረፈም” ሲሉ አርሶ አደሩ ማሬ ታረቀኝ ለአሚኮ ተናግረዋል። የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያው ጥላሁን ዓለም ለአሚኮ እንደገለጹት ከ600 በላይ አርሶ አደሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በፍጥነት መልሶ የማቋቋም ሥራ መሠራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የደረሰው ጉዳት ከባድ በመኾኑ አርሶ አደሮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በመሥራት በበጋ መስኖ ሰብል ልማት ምርቱን እንዲያካክሱ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በዕውቀት አየነው ተናግረዋል። ኀላፊው በሌሎችም ቀበሌዎች ተመሳሳይ ጉዳት ሊያጋጥም ስለሚችል አርሶ አደሮቹ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ሊሰበስቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦችም ሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አርሶ አደሮችን መልሶ በማቋቋም ሥራው ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!