
ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 (አሚኮ) የንግድ ፈጠራ ሥራ ባለቤቶችን የማጠናከር እና የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሥራ እና ክሕሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል። ዓለም ዓቀፍ የንግድ ሥራ ፈጣሪዎች (ኢንተርፕርነርሺፕ) ሳምንት “ኢንተርፕርነርሺፕ ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 9/2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሔድ ቆይቷል።
የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንቱ በዓለም ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ ተከብሯል። ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ አካላት በቀጥታ እና በበየነ መረብ ተሳትፈዋል፡፡ የፓናል ውይይቶች፣ አውደ ርዕዮች፣ ኮንፈረንሶች፣ ሴሚናሮች፣ የእርስ በእርስ ትውውቅ እና የልምድ ልውውጦች የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንቱ አካል ነበሩ፡፡
የበዓሉ የመዝጊያ መርሐ ግብር የሥራ እና ክሕሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በተገኙበት ትናንት ማምሻውን ተከናውኗል። በመድረኩ በተለያዩ የሥራ ፈጠራ ዘርፎች ተወዳድረው ብልጫ ያስመዘገቡ የዓመቱ ምርጥ ሥራ ፈጣሪዎች ከሥራ እና ክሕሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እውቅና ተበርክቶላቸዋል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት፣ “ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በምታደርገው ርብርብ የኢንተርፕርነሮች ሚና ወሳኝ ነው” ብለዋል፡፡
በርካታ የዓለም ሀገራት ችግሮችን ተሻግረው ከሃብት ማማ የደረሱት ለሥራ ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታቸው መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ለሥራ ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን እና በዚህም አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል። ዜጎች ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት እና የፋይናንስ ክፍተቶቻቸውን የሚሞሉበት ምቹ ኹኔታ መፈጠሩን ነው ያስረዱት፡፡
አኹን ላይ በርካታ ዜጎች ከሥራ ጠባቂነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት በመሸጋገር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አማራጭ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን አመላክተዋል። በቀጣይም የንግድ ፈጠራ ሥራ ባለቤቶችን የማጠናከርና የመደገፍ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ እውቅና የተሰጣቸው አካላት በቀጣይም ጠንክረው በመሥራት የድርሻቸውን ሀገራዊ ኀላፊነት እንዲወጡም አደራ ብለዋል።
የዜጎችን የሥራ ፈጠራ ከህሎት በሥልጠና በማጎልበት ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ሚና ጉልህ እንደነበር ጠቅሰዋል። የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሐሰን ሁሴን (ዶ.ር) ሰዎች ክሕሎታቸውን አውጥተው ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ ሥልጠና መስጠት ከኢንስቲትዩቱ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የዜጎችን የክሕሎት ክፍተት ለመሙላት አሁን ላይ በመላው ሀገሪቱ 5 ሺህ 600 አሠልጣኞች መመደቡን ገልጸዋል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ 500 ሺህ ለሚኾኑ ዜጎች የክሕሎት ማሳደጊያ ሥልጠና መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
እውቅና የተሰጣቸው የዓመቱ ምርጥ ሥራ ፈጣሪዎች እውቅናው ለቀጣይ ሥራቸው አቅም እንደሚኾናቸው ገልጸው፤ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!