“የተማመኑ ታላቅ ታረክ ሠርተዋል፤ ሀገርንም አኩርተዋል”

59

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሚተማመኑ ጓደኛሞች ፍቅራቸው እስከ መቃብር ነው፡፡ መቃብርም አያስቀረውም ከዚያ አልፎም ይሻገራል፡፡ ከመቃብር በላይም ለታሪክ ተቀምጦ ሲነገር ይኖራል፡፡ የተማመኑ ሀገርን አስከብረዋል፡፡ የተማመኑ ችግሮቻቸውን በሰላም እና በፍቅር ፈትተዋል፡፡ ሀገርን አኩርተዋል፡፡ የጋራ እና ታላቅ ታሪክ ሠርተዋል፡፡

የተማመኑ ኢትዮጵያውያን በአንድ የንጉሥ ቃል ተጠርተው ከጫፍ ጫፍ ተነስተዋል፡፡ የተማመኑ ኢትዮጵያውያን በአንዲት ሠንደቅ ዓላማ ተሠባሥበው ለነጻነት ተሰውተዋል፡፡ ለሉዓላዊነት መስዋዕት ኾነዋል፡፡ ንጉሡ ሕዝባቸውን፣ ሕዝቡም ንጉሳቸውን ያምናሉና ለአንድ ዓላማ በአንድነት ተነስተው ዘላለማዊ ታሪክ ጽፈዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ያ የጣሊያን ተላላኪ ኮንቲ አንቶኖሊን የውጫሌን ውል አልቀበልም ሲሉት ዝቶ ሲወጣ “ጦርነቱን የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ በዚህ የሚደነግጥልህ የለም፡፡ ሂድ የፎከርክበትን አድርግ፡፡ እኛም የመጣውን እናነሳዋለን፡፡ እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ሀገሩን የማያድን ሰው በዚህ የሌለ አይምሰልህ፡፡ የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ ሀገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጂ ሞት አይባልም፡፡ አሁንም ሂድ አይምሽብህ፤ የፈከርክበትን በፈቀደህ ጊዜ አድርገው፡፡እኛም ከዚህ እንቆይሃለን” ያሉት በሀገራቸው ሕዝብ ሥነ ልቡና፣ በሀገር ወዳድነቱ፣ በጀግንነቱ፣ የንጉሥን ቃል አክባሪነቱ፣ ለነጻነት ቀናዒነቱ፣ ለሉዓላዊነት ከፊት ተሰላፊነቱ ስለሚተማመኑ ነው፡፡

ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ወረኢሉ ላይ ከተህ ጠብቀኝ ብለው አዋጅ ያስነገሩት፣ ድልም እንደሚያደርጉ የተማመኑት፣ በልበ ሙሉነትም የተናገሩት ቃላቸውን የሚያክብር፣ ለቃሉም የሚታመን፣ ለሀገሩ እና ለሠንደቁ ለመሞት የማያቅማማ ሕዝብ እንዳላቸው ስለተረዱ ነው፡፡ ስለሚያምኑት እና ስለሚያምናቸውም ነው፡፡ ወንድም ከወንድም፣ ጓደኛ ከጓደኛ፣ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ፣ ማኅበረሰብ ከመንግሥት፣ መንግሥት ከማኅበረሰብ መተማመን እና ልክን መተዋወቅ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን አርበኞች ዱር ቤቴ ብለው በራሳቸው ትጥቅ እና ስንቅ ጣሊያንን ለመዋጋት በረሃ የወረዱት፣ በሩቅ ሀገር ያለውን ንጉሳቸውን ቃል ያከበሩት በመካከላቸው መተማመን እና ቃል ኪዳን ስላለ ነበር፡፡ በረሃ ገብተው ድል እንደሚመቱ ይተማመኑ ነበር፡፡ የንጉሡ በዙፋን መኖር እና አለመኖር በመካከላቸው ያለውን መተማመን እና ቃል ኪዳን አላሸከረውም፡፡ ለአንዲት ሀገር የመቆማቸውን ነገርም አላዛባውም፡፡

ለኢትዮጵያዊነት ያላቸውን ቀናኢ መንፈስም አላጠፋውም፡፡ ይልቁንስ ድል አድርገው የሚገናኙበትን ቀን ያስናፍቃቸው ነበር፡፡ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ጽኑ ሀገርን ይሠራል፡፡ አንድነትን ያጠናክራል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው እና በሠንደቃቸው ላይ ተማምነው እና ተግባብተው በአንድነት ኖረዋል፡፡

እየኖሩም ነው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ሥር መስደድ ከጀመረ ወዲህ ግን በጋራ ጉዳዮች ተማምኖ ከመሥራት ይቅል መነቃቀፍ፣ አለመተማመን፣ ለመፍትሔ ከመዘጋጀት ይልቅ ለመነቃቀፍ እና ለመተቻቸት መሯሯጥ በርክቷል፡፡ ለታላቋ ሀገር በጋራ ከመትጋት ይልቅ በአካባቢ እና በአካባቢ ብቻ መወሰን፣ ሁሉንም በጥርጣሬ የማየት አዝማሚያ በዝቷል፡፡ መተማመን እና መተሳሰብ ተሸርሽሯል፡፡

የታሪክ እና የባሕል ምሁሩ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ትችት እና ስድብ ገንዘብ ስለኾነ እንደ ኑሮ መግፊያ እንደ መተዳደሪያ እየተቆጠረ ነው ይላሉ፡፡ በስድብ እና በትችት ወገኔን ጎዳሁ ወይስ ጠቀምኩ ሳይኾን እኔ እጠቀማለሁ ወይስ አልጠቀምም የሚለው ሃሳብ ከቀደመ እንቸገራለን ነው የሚሉት፡፡

ይህ አካሄድ ደግሞ በእጅጉ ይጎዳል ይላሉ፡፡ የግል ጥቅምን መሠረት ያደረገ አካሄድ ደግሞ የጋራ የኾኑ ጉዳዮችን ይጎዳል፡፡ ስድብ እና ትችት ብቻ ገበያ ሲወጡ ለሸቀጦቹ ጀሮ ባለመስጠት መቅጣት ያለበት ሕዝቡ ነው፡፡ ሁልጊዜ ከመተቸት እና ከመሳደብ ይልቅ መፍትሔ ማምጣት፣ አካሄዱን ማመላከት ይገባል ነው የሚሉት፡፡

ሂስ ሙያዊ ሲኾን እና ሂስ ለሚደረገው እና ለሀገር የሚጠቅም ከኾነ ማድረግ የተገባ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ከራስ ጥቅም አንጻር ብቻ መመዘን ከኾነ እና ስድብ ብቻ ከኾነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ መጠራጠርን፣ ጎራ ለይቶ መሰዳደብን ሊያስቀረው የሚችለው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንደኾነም ፕሮፌሰሩ አንስተዋል፡፡

እንደ ምሁሩ ገለጻ በአንድ ቀን ሁሉም ነገር እንዳልተበላሸ ሁሉ በአንድ ቀን ሁሉም ነገር አይሰተካከልም፡፡ ችግሮችን መተማመን ላይ በተመሠረተ ውይይት መፍታት እንጂ ሁልጊዜ በጦርነት ለመፍታት መሞከር አይጠቅምም፡፡ ምክንያቱም በጦርነት ወደ ሥልጣን የመጣ ወይም በጦርነት ችግሮቹን የፈታ የሚመስለው መጨረሻ ላይ የሚወገደው በጦርነት ነውና ይላሉ፡፡

የሥልጣን ጥማት መተማመን እና ሰላምን ያጠፋል፡፡ ለሀገር መፍትሔ ማስቀመጥ፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት ሲቻል መተማመን በሂደት ይጠነክራል ነው የሚሉት፡፡ ሁልጊዜም መጠራጠር ካለ መተማመን አይኖርም፡፡ መተማመን ውስጥ መጠራጠር ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን እየተጠራጠርን በሂደት መተማመንን መገንባት አለብን ብለዋል፡፡

መተማመን የሚመጣው መጀመሪያ ችግሮች ላይ የጋራ መረዳት ሲኖር ነው ይላሉ፡፡ ሁሉንም የሚያስተማምን አሥተዳደር ለመገንባት መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ለአምስት ዓመት እንዲመራ የመረጥነው አካል የተሰጠውን ዓመት እስኪያጠናቅቅ ድረስ የምንደግፈው እንጂ በነገታው የምንክደው መኾን የለበትም፡፡

ይሄ ከኾነ ግጭቱ እና ጭቅጭቁ እየሰፋ ይሄዳል እንጂ ችግሩ አይፈታም ነው የሚሉት፡፡ ዛሬ የመረጥነውን ሰው ነገ የምንክደው ከኾነ መጀመሪያ ለምን መረጥነው ብለን ራሳችን መጠየቅ አለብን፣ የመረጥነውን መደገፍ እና ለችግሮች የጋራ መፍትሔ መስጠት ይጠበቃል ይላሉ፡፡ መጋደል የሚጠቅመን ቢኾን ኖሮ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ በብዙ መንገድ ትጠቀም ነበር፤ ሰላም የሚያመጣም ቢኾን ኢትዮጵያ እስካሁን ሰላም ይመጣላት ነበር፡፡

ነገር ግን ይሄ አልኾነም በአንደኛው ጦርነት የሞቱት ሰዎች ሳንቀብር፣ ለወገኖቻቸው ሳናረዳ ወደ ሌላ ጦርነት መግባት የተገባ አይደለም ነው የሚሉት፡፡ ችግሮቻችን በውይይት መፍታት ሲቻል በጦርነት ለመፍታት ተነስተን ብዙ ሰዎችን አጣን፣ ያጣናቸው ሰዎች ችግሮቻችን የሚፈቱልን፣ ሰላማችን የሚያመጡልን እና የሚያሳድጉን በኾነ ባልከፋ ነበር ነገር ግን ይሄን ማድረግ አይቻልም ይላሉ፡፡

በተከታታይ እየተደረጉ ያሉ ጦርነቶች ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን አልጠቀመም፡፡ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ምን እንደሚያገኝ አይገባኝም? ነው የሚሉት፡፡ ጥይት እየገዙ ከመገዳደል ይልቅ፣ እየተወያዩ ማልማት ይበልጣል፡፡ ማነው የሚያዋጋን ? ምንድን ነው የሚያዋጋን? የሚለውን መጠየቅ እና መመለስ ይጠበቃልም ይላሉ፡፡

ለሰላማዊ ሂደት ቅድሚያ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡ በጥይት የሚመጣ ሥልጣን በጥይት ይወርዳል፣ የማያበራ አዙሪት ውስጥ ነው የሚከተው፡፡ በውይይት የሚመጣ ግን በውይይት ነው የሚጸናው ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ነገር ግን ለታሪኳ የሚመጥን ሥራ እየሠራንላት አይደለም ነው የሚሉት፡፡ ከችግሮቻችን ለመውጣት ከግጭት ይልቅ ሰላምን ማስቀድም፣ በውይይት ማመን፣ እልህን መተው፣ ሰከን ብሎ ማሰብ እና ለጋራ ሀገር የጋራ የኾኑ ጉዳዮችን መሥራት ይገባል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግብራቸውን በአግባቡ እንዲከፍሉ መንግሥት የንግድ ሕጉን እንዲያስከብር ነጋዴዎች ጠየቁ፡፡
Next articleለሥራ ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ አበረታች ውጤት ተገኝቷል።