ግብራቸውን በአግባቡ እንዲከፍሉ መንግሥት የንግድ ሕጉን እንዲያስከብር ነጋዴዎች ጠየቁ፡፡

27

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ግብራቸውን በአግባቡ እንዲከፍሉ መንግሥት የንግድ ሕጉን እንዲያስከብር አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ነጋዴዎች ጠይቀዋል፡፡ አቶ ጥላሁን ታየ በወረታ ከተማ ሆቴል ሥራ የቫት ተመዝጋቢ ነጋዴ ናቸው። የሒሳብ መዝገብ በመያዝ ይሠራሉ። ግብር መክፈል ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት አቶ ጥላሁን ዘመናዊ ግብር አከፋፉልን ለመተግበር ግብር ከፋዩ ብቻ ሳይኾን ከሰብሳቢው አካልም የሚጎድል ነገር እንዳለ ነው ያነሱት፡፡

ወይዘሮ ፍቅርአዲስ ጌትነት የሞሐ ለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ ወኪል ናቸው። ግብር አንድ ሰው ላገኘው አገልግሎት የሚከፍለው እና መንግሥት ደግሞ የጋራ መጠቀሚያ ልማት የሚሠራበት ገንዘብ ነው ብለዋል። መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ተቋማት እና መሰል መሠረተ ልማቶች የሚገነባበት እና በወል የምንጠቀምበት ሃብት መኾኑንም ተናግረዋል።

የንግዱ ማኅበረሰብ የሚያነሳቸው የፍትሐዊነት እና የግብር ጥናት ጥያቄ ተገቢነት የሚኖራቸው ጊዜ እንዳለም ገልጸዋል። ገቢ እና ወጪ በመዝገብ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቢኾን ሁለቱንም ችግር እንደሚፈታም ተናግረዋል። የንግድ ሥርዓቱ የበለጠ መዘመን እና መጠናከር አለበት ነው ያሉት፡፡ የባለፈው ዓመትን ግብር ከፍለው ማጠናቀቃቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ፍቅርአዲስ የዘንድሮውንም በመዝገብ በመሥራት ሕግ አክብረው እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት።

የንግዱ ማኅበረሰብም የደኅንነት ስጋት የሚቀረፍለት ግብሩን በትክክል በመክፈል እና ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ለልማት አስተዋጽኦ ለማበርከት ጤናማ የንግድ ሥርዓት መከተል እንደሚገባውም ተናግረዋል። ተገዶ ሳይኾን አምኖበት የንግድ ሒሳብ መያዝ እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ ከንግዱ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይኾን ከግብር ሰብሳቢውም መስተካከል ያለባቸው ችግሮች እንዳሉ አመላክተዋል። በቂ ግንዛቤ አለመፍጠር፣ ትክክለኛ ጥናት አለማድረግ፣ የሥነ ምግባር ጉድለት ያለባቸው ባለሙያዎች መኖር፣ ፍትሐዊ ያልኾነ የግብር አወሳሰን፣ ወደ ንግድ መረቡ ያልገቡ ነጋዴዎች መኖራቸው እና ሕገ ወጥ ነጋዴን አለመቆጣጠር ከግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ማስተካከል ያለበት እንደኾነ አመላተዋል፡፡

የወረታ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበበ አስማረ የከተማ አሥተዳደሩ ግብር ሰብሳቢ እና ከፋዩ ማኅበረሰብ ጥሩ መሥተጋብር እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ አዲሱ የግብር ጥናት እና የጸጥታ ችግሩ ግብርን ለመሰብሰብ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል። የችግሩን መኖር ግምት ውስጥ አስገብተን የነጋዴዎችን ቅሬታ እና ይግባኝ እየሰማን ምላሽ በመስጠት እየሠራን ነው ብለዋል።

በከተማው በ2017 በጀት ዓመት 471 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም አስታውቀዋል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 76 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል። የግብር አሰባሰቡ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡ ግብር ከፋዮች የሚያነሱትን ቅሬታ በመስማት ተነጋግሮ እና ተግባብቶ የመሥራት ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችንም ወደ ሕጋዊነት ለማምጣት እንሠራለን ነው ያሉት።

እቃዎችን እያዞሩ የሚሸጡ ሰዎችን የግንዛቤ ፍጠራ ሥልጠና በመስጠት፣ ወደ ሕጋዊ ንግድ ሥርዓት በማስገባት፣ በሼድ እንዲሠሩ እና ተገቢ ግብር እንዲከፍሉ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡ የደቡብ ጎንደር ዞን ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ዓባይነው ኃይሉ በዞኑ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ግብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ዜናው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 426 ሚሊየን 416 ሸህ ብር መሰብሰቡንም አስታውቀዋል፡፡ የተሰበሰበው ገቢ የዕቅዱ 15 በመቶ መኾኑን አመላክተዋል፡፡

ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በመወያየት ግብር ለሠሩበት እና ላተረፉበት የሚከፈል የዜግነት ኀላፊነት መኾኑን በማስረጽ ላይ ነን ብለዋል ኀላፊው፡፡ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት አልሠራንም የሚሉ ግብር ከፋዮችም አለመሥራታቸውን የሚገልጽ የንግድ ሒሳብ መዝገባቸውን በማሳየት የተጣለባቸውን ግብር ማስተካከል እንደሚችሉ አስታውቀዋል። የቁርጥ ግብር ከፋዮችን ደግሞ ችግሩን በመረዳት መፍትሄ እየሰጠን ነው ብለዋል።

ንግድን ሥርዓቱ በሚያዝዘው መሠረት መፈጸም፣ ግብርንም በወቅቱ እና በታማኝነት መክፈል ለሀገር ልማት፣ ሠላም እና እድገት ወሳኝ መኾኑን ግብር ከፋዮች እና ግብር ሰብሳቢው አካል ይጋሩታል። መንግሥት ሕግ ያስከብርልን፤ እኛ ግብራችን እንከፍላለን ነው ያሉት አስተያየታቸውን የሰጡ ግብር ከፋዮች።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግብርን እንደ ዕዳ መቁጠር ለገቢ አሠባሠብ እንቅፋት ኾኗል።
Next article“የተማመኑ ታላቅ ታረክ ሠርተዋል፤ ሀገርንም አኩርተዋል”