
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ በ2017 በጀት ዓመት ከ947 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር ለመሠብሠብ አልሞ እየሠራ መኾኑን የአሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ አሳውቋል። መምሪያው እስከ ኅዳር 13/2017 ዓ.ም ድረስ ከመደበኛ ገቢ 250 ሚሊዮን ብር መሠብሠቡን የመምሪያው ግብር አሠባሠብ እና አወሳሰን ክትትል ዋና የሥራ ሂደት መሪ ሙሉጌታ አበራ ተናግረዋል፡፡
የሥራ ሂደት መሪው ከከተማ አገልግሎት 309 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር መሠብሠቡንም ነው ያብራሩት። መምሪያው እስከ አሁን የዕቅዱን 28 በመቶ ሠብሥቧል ነው ያሉት። በቀሪ ወራት ዕቅዱን ለማሳካት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ አኹንም በግብር አሠባሠብ ዙሪያ በርካታ ችግሮች እየገጠሟቸው መኾኑን አንስተዋል።
ከችግሮቹ መካከልም:-
👉 የንግዱ ማኅበረሰብ ግብርን የልማት ምንጭ ከማድረግ ይልቅ ዕዳ ነው ብሎ መቁጠር
👉 በአሥተዳደሩ በአንዳንድ ወረዳዎች ያለው የጸጥታ ችግር የአሥተዳደሩ እና የወረዳ ባለሙያዎች በአግባቡ ግብርን ለመሠብሠብ መቸገራቸው
👉 የአጋር እና የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ችግር መኖሩን ጠቅሰዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ እነዚህ ችግሮችን በማቃለል ዕቅዱን ለማሳካት ለንግዱ ማኅበረሰብ የግብር ትምህርት በትኩረት እየሠጠ ስለመኾኑም አቶ ሙሉጌታ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ ያለደረሠኝ ሽያጭ ሲያከናውኑ በነበሩ 23 ነጋዴዎች ላይም እስከ 50 ሺህ ብር የቅጣት ርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።
የአደጉ ሀገራት የዕድገታቸው መሠረት ዜጎቻቸው ሠርተው ካገኙት ገንዘብ በኀላፊነት ስሜት ግብር በወቅቱ ስለሚከፍሉ እንደኾነም ተናግረዋል። መንግሥታቸውም ዜጎች በከፈሉት ግብር ሀገራቸውን አልምተው ሃብታም ሀገራት ለመባል በቅተዋል ነው ያሉት። የእነዚህ ሀገራት ዜጎች ግብር የልማታቸው ምንጭ አድርገው ይወስዳሉ፤ በኢትዮጵያም ይህ ባሕል ኾኖ እንዲታይ ብርቱ ጥረት ያሻል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!