የሰላሙ ኹኔታ መሻሻል በማሳየቱ የግብር አሠባሠቡ ተነቃቅቷል።

29

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ከሚገኙ የልማት ቀጣናዎች ምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። ዞኑ በእርሻ ልማት እና ሌሎች የሥራ ዘርፎች የተሠማሩ ግብር ከፋዮች መገኛ ቢኾንም በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የሚጠበቀውን ግብር መሠብሠብ አለመቻሉን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ደብሬ ብርሃኑ ገልጸዋል።

ተወካይ ኀላፊዋ እንዳሉት በ2017 በጀት ዓመት በዞኑ 859 ሚሊዮን 632 ሺህ 399 ብር ገቢ ለመሠብሠብ እየተሠራ ይገኛል። እስከ ሕዳር 16/2017 ዓ.ም 166 ሚሊዮን 608 ሺህ 534 ብር ተሠብሥቧል። ከዚህ ውስጥ 152 ሚሊዮን 264 ሺህ 752 ብር ከመደበኛ ገቢ የተገኘ ሲኾን 14 ሚሊዮን 343 ሺህ 782 ብር ደግሞ ከአገልግሎት ገቢ የተሠበሠበ መኾኑን ተናግረዋል።

እስከ አኹን የእቅዱን 47 በመቶ መሠብሠብ የሚጠበቅ ቢኾንም በዞኑ ባለው የሰላም ችግር ምክንያት የተሠበሠበው ገቢ ከ19 በመቶ አይበልጥም። በዞኑ በአራት ወረዳዎች እና በሦስት ከተሞች ግብር መሠብሠብ የሚጠበቅ ቢኾንም መሠብሠብ የተቻለው ግን በሦስቱ ከተሞች ብቻ መኾኑን ነው የገለጹት።

በተለይም በቋራ ወረዳ ተቋሙ ጭምር በመውደሙ ግብር ለማስከፈል ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል። በተያዘው ወር የሰላሙ ኹኔታ መሻሻል በማሳየቱ የግብር አሠባሠቡ መጨመር ማሳየቱንም ገልጸዋል። ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በአካባቢያቸው በሚገኝ ባንክ፣ በቴሌ ብር እና ሌሎች አማራጮች እንዲከፍሉ አሣሥበዋል። በዞኑ 9 ሺህ 809 ግብር ከፋዮች እንደሚገኙ የመምሪያው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማኅበረሰቡ ለማንነቱ እንደሚያደርገው ትግል ሁሉ ለገቢም ትኩረት ሰጥቷል።
Next articleኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን በውጤታማ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡