ማኅበረሰቡ ለማንነቱ እንደሚያደርገው ትግል ሁሉ ለገቢም ትኩረት ሰጥቷል።

19

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የውስጥ ገቢን በመጠቀም የልማት ሥራዎችን የሚሠራ ዞን ነው፡፡ ዞኑ የውስጥ አቅምን በመጠቀም የልማት ሥራዎችን በመሥራት በአርዓያነት የሚጠቀስ ይጠቀሳል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ ጌታቸው አብርሃ በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት 756 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሠብሠብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 153 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መሠብሠቡንም ገልጸዋል፡፡ የገቢ አሠባሠቡን ሥራ ስኬታማ ለማድረግ ተጨማሪ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑም ገልጸዋል፡፡ በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የነበረው የጸጥታ ችግር እና የአፈጻጸም ችግሮች ገቢን በተገቢው መንገድ ለመሠብሠብ ፈተና ኾኖባቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

አኹን ላይ ችግሩ መስተካሉን እና በቀጣይ የገቢ አሠባሠብ ሥራዎች እንደሚሠሩም አመላክተዋል፡፡ በአካባቢው ያለውን አቅም መሠረት ያደረገ የገቢ አሠባሠብ ሥርዓት እንዲኖር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ገቢ ከልማት በላይ መኾኑን የገለጹት ኃላፊው “ገቢያችን ለሕልውናችን” በሚል መሪ ሃሳብ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ማኅበረሰብ ለማንነቱ እንዳደረገው እና እንደሚያደርገው ትግል ሁሉ ገቢም የሕልውና ጉዳይ ነው በሚል በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የውስጥ ገቢን በመሠብሠብ የልማት ሥራዎችን መተግበር ይገባል ነው ያሉት፡፡ ዞኑ በውስጥ ገቢ የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በውስጥ ገቢ በከተሞች የጌጠኛ መንገዶች፣ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ መንገዶች፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የገለጹት፡፡

“በጀታችን ራሳችን ነን” በሚል ገቢን ከሕልውና ጋር አያይዘን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ የቁርጥ ግብር ጥናት በማድረግ የነበሩ ችግሮችን ለማሻሻል ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ገቢ መሠብሠብ ለገቢዎች መምሪያ ብቻ ሳይኾን ለሁሉም ተቋማት እና መሪዎች ኃላፊነት የሚሰጥ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

የዞኑ ትልቅ ሃብት የእርሻ ሥራ ነው ያሉት ኃላፊው የእርሻ ሥራ ግብር በትልቁ ያልሠራንበት ነው ብለዋል፡፡ በሁለተኛው ሩብ ዓመት የእርሻ ሥራ ግብር የትኩረት አቅጣጫ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የመሬት አገልግሎት ግብር ላይ ያለውን ክፍተት ለመፍታት እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ገቢ ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሕልውና እና የሰላም ጉዳይ ነው ያሉት ኀላፊው ማኅበረሰቡ ለገቢ አሠባሠብ ሥርዓቱ ይበልጥ ደጋፊ እንዲኾ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የታቀደው እቅድ እንዲሳካና የልማት ሥራዎች በስፋት እንዲሠሩ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገር ያለ ገቢ ምንም መኾኗን ተረድተን በመሥራታችን ባቀድነው ልክ መራመድ ችለናል” የደቡብ ወሎ ዞን ገቢዎች መምሪያ
Next articleየሰላሙ ኹኔታ መሻሻል በማሳየቱ የግብር አሠባሠቡ ተነቃቅቷል።