“ሀገር ያለ ገቢ ምንም መኾኗን ተረድተን በመሥራታችን ባቀድነው ልክ መራመድ ችለናል” የደቡብ ወሎ ዞን ገቢዎች መምሪያ

33

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በገቢ አሰባሰብ ላይ ጫና አሳድሯል፡፡ ክልሉ ባቀደው ልክ ገቢ ለመሰብሰብ ፈተናዎች ገጥመውት ቆይተዋል፡፡ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ የገቢ አሰባሰብ ሥራው በጥሩ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡
በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ፈተና ቢኾንበትም ችግሮችን ተቋቁሞ መሥራት በመቻሉ በታቀደው ልክ ገቢ እየተሰበሰበ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታውቋል።

በዞኑ ውስጥ በሩብ ዓመቱ መሰብሰብ ካለባቸው ዕቅድ በላይ የተራመዱ ወረዳዎችም አሉ ነው የተባለው። የወረባቦ ወረዳ በገቢ አሰባሰቡ ግንባር ቀደም ከኾኑት ውስጥ አንዱ ነው። የወረዳው ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይማም እንድሪስ በወረዳው ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

እስከ ኅዳር ወር አጋማሽ ድረስ ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰባቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የተሰበሰበው ገቢም በዚህ ወቅት ለመሰብሰብ ካቀዱት በላይ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ገቢዎች መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ታረቀኝ ተፈራ ዞኑ በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በዞኑ 45 ሺህ 131 ግብር ከፍዮች አሉ ያሉት ኅላፊው እስካሁን ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰብስበናል ነው ያሉት።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀዱት ውስጥ 31 ነጥብ 31 በመቶ የሚኾነውን ገቢ መሰብሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ በፈተና ውስጥም ኾነው ጥሩ አፈጻጸም እንዳላቸው ነው የተናገሩት። ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ማማከራችን፣ ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር ተቀራርበን መነጋገራችን፣ አጋር አካላትን ማሳተፋችን እና ከተቋሙ ባለሙያዎች ጋር በጥልቀት መወያየታችን የውጤታማነታችን መሠረቶች ናቸው ብለዋል።

“ሀገር ያለ ገቢ ምንም መኾኗን ተረድተን በመሥራታችን ባቀድነው ልክ መራመድ ችለናል” ያሉት ተወካይ ኅላፊው አሁንም ድረስ በጸጥታ ችግር ምክንያት ገቢ ያልተሰበሰበባቸው አካባቢዎች እንዳሉም ጠቁመዋል። የታጠቁ ኃይሎችን በመፍራት በድብቅ ግብራቸውን የሚከፍሉ ታማኝ ነጋዴዎች መኖራቸውንም አንስተዋል። እኒህ ነጋዴዎች በፈተና ውስጥ ሆነው ለሀገራቸው የታመኑ ናቸው ብለዋቸዋል።

በዓመቱ ለመሰብሰብ የታቀደውን ማሳካት እንደሚችልም አመላክተዋል። በተግዳሮት ውስጥም ኾነው ለሀገራቸው የሚታትሩ የዞኑ የገቢ ሰብሳቢ ባለሙያዎች ምስጋና ይገባቸዋልም ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በውስብስብ ችግሮች ውስጥ ሆነን የሰበሰብነው ገቢ መጠኑ ቢያንስም የጽናታችን ምልክት ነው” የምሥራቅ ጎጃም ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ገነት በቀለ
Next articleማኅበረሰቡ ለማንነቱ እንደሚያደርገው ትግል ሁሉ ለገቢም ትኩረት ሰጥቷል።