
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጸጋው ልክ ገቢ ያልሰበሰበ ሀገር በሕዝቦች ፍላጎት ልክ የሞላ ልማት ለመሥራት ይቸገራል። የነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልስ መሰረተ ልማት ለመገንባት የሚያልም ክልልም የውስጥ ገቢውን አጠናክሮ መሰብሰብ ግድ ይለዋል። ሀገሩ አስፈላጊውን የልማት ፍላጎት እንድታሟላ የፈለገ ዜጋ ሁሉ ሠርቶ ከሚያገኘው ገቢ ቀንሶ ግብር መክፈል ግድ ይለዋል። ከሀገሬው ዜጎች ካልተሠበሠበ በስተቀር በመንግሥት ብቻ ሊመነጭ የሚችል በቂ ሀብት አይኖርምና።
ሀገር በቂ ገቢ ኖሯት፤ መንግሥትም አስፈላጊውን ልማት ይዘረጋ ዘንድ ሰላምን አስፍኖ ተዘዋውሮ መሥራት፣ የገቢ ግብርንም በወቅቱ መክፈል ከዜጎች ይጠበቃል። ምሥራቅ ጎጃም ዞን እንደ አብዛኞቹ የአማራ ክልል አካባቢዎች ሁሉ የጸጥታ ችግር ገጥሞት ከርሟል። ይሁን እንጅ ገቢ ለዞኑ ልማት ያለውን ወሳኝነት በመረዳት በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ገነት በቀለ እንዳሉት በ2017 በጀት ዓመት በዞኑ ዕቅድ ከ3 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው። የሩብ ዓመት ክንውኑን ስንመለከት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 606 ሚሊየን 789 ሺህ 346 ብር ተሰብስቧል።
የእቅዱን 18 ነጥብ 8 በመቶ ማለት ነው። ከዚህ ውስጥ 548 ሚሊየን 35 ሺህ 683 ብሩ ከመደበኛ ገቢ የተገኘ ሲኾን 58 ሚሊየን 753 ሺህ 663 ብር ደግሞ ከከተማ አገልግሎት የተሰበሰበ ነው። መምሪያ ኀላፊዋ እንዳሉት የዘርፉ የአገልግሎት አሠጣጥን በማዘመን ገቢ እየተሠበሰበ ነው። የሚቀርቡ የግብር በዛብኝ አቤቱታዎች ፈጣን ምላሽ ይሰጣቸዋል። ተገቢ ጥያቄ ያላቸው ይስተካከልላቸዋል፤ ተገቢነት የሌለው ጥያቄ ያቀረቡትም ውሳኔውን ተቀብለው በወቅቱ እንዲከፍሉ ይደረጋል።
እንደ ዞን 4 ሺህ 271 ግብር ከፋዮች የግብር ቅሬታ አቅርበው 4 ሺህ 132 የሚኾኑት ተገቢውን ምላሽ አግኝተዋል። ይህም ለ96 በመቶው ፈጣን ምላሽ ተሰጥቷል ማለት ነው። መምሪያ ኀላፊዋ ገነት በቀለ እንዳሉት አሁን ላይ ግብር ከፋዩ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደ ገቢ ተቋሙ በመምጣት ቅሬታና ይግባኝ በማቅረብ በሚሰጠው ምላሽ መሰረት የሚጠበቅበትን የግብር ግዴታ እየተወጣ ነው። ግብርን አውቆ በጊዜ መክፈል የሥልጡንነት መገለጫ ነው፤ ሁሉም ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በመክፈል ለሀገር እና ሕዝብ ያለውን ፍቅር ይግለጽ ነው ያሉት ወይዘሮ ገነት።
የዞኑ ገቢዎች መምሪያ እና የተዋረድ ተቋማትም የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ፈጣን ምላሽ በመስጠት የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ከማድረግ አኳያ የሚበረታታ ተግባር እየፈጸሙ ነው ብለዋል ኀላፊዋ። ይሁን እንጂ የታቀደውን ያህል ገቢ አልተሰበሰበም። ለዚህ እንደምክንያት ከተነሱ ችግሮች መካከል:-
👉 የፀጥታ ችግር በመኖሩ የተቋሙ ሠራተኞች በሚፈለገው ልክ ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻላቸው፣ 👉 ቅንጅታዊ አሠራር በሚፈለገው ልክ ባለመጠናከሩ በተለይም የከተማ አገልግሎት የገቢ አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑ እና
👉 ውዝፍ ገቢ በሚፈለገው ልክ አለመሰብሰብ በዋናነት ተነስተዋል።
በውስብስብ ችግሮች ውስጥ ሆነን የሰበሰብነው ገቢ የጽናታችን ምልክት ነው ያሉት ወይዘሮ ገነት በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት በእቅድ ልክ ለመፈጸም እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ የታቀደውን ለመፈጸም እንቅፋት የኾኑ ችግሮችን በጥልቅ ስለመገምገማቸውም ተናግረዋል። ችግሮች ተቀርፈው ለሀገር እድገት መሰረት የኾነው የግብር ገቢም እንዲሠበሠብ ጥብቅ የድጋፍና ክትትል ሥራ ይከናወናል፤ ለዚህም በዞን ደረጃ ጠንካራ ሥርዓት ተዘርግቷል ነው ያሉት ያሉት። የዞኑ ነዋሪዎችም ያለገቢ ሊሠራ የሚችል የልማት ሥራ እንደማይኖር በመገንዘብ ለዘርፉ አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል መምሪያ ኀላፊዋ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!