
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አራጋው ሽወሽ በሰሜን ሸዋ ዞን የደረጃ ለ ግብር ከፋይ ናቸው ባለፉት ጊዜያት ሥራ መሥራት ባለመቻላቸው ግብር መክፈል እንዳልቻሉ ነግረውናል፡፡ አቶ አራጋው የግብር ጠቀሜታን ብንረዳም ወቅታዊው የሰላም ኹኔታ የሚጠበቅባቸውን የግብር አስተዋጽኦ በሥራቸው ልክ መክፈል እንዳልቻሉ ነው የሚገልጹት፡፡
ነጋዴው እንደሚሉት የሚኖሩበት ከተማ በራሱ ገቢ የሚተዳደር እንደኾነ እና በከተማው የሚሠሩ የልማት ሥራዎችም እሳቸው እና ሌሎች ዜጎች በታማኝነት ካገኙት ገቢ ላይ በሚከፍሉት የግብር ገቢ እንደሚሠራ ተረድተው ከዚህ በፊት ግብራቸውን ይክፍሉ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ኹኔታ ግብር ለመክፈልም ኾነ በከተማቸው የልማት እንቅስቃሴ ላይ መሳተፍ እንዳላስቻላቸው ገልጸዋል። አኹን ላይ የተሻለ ነገር ስላለ ሠርተው ካገኙት ገቢ ላይ ግብር መክፈላቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በሰሜን ሽዋ ዞን አሥተዳደር የገቢዎች መምሪያ የግብር ትምህርት እና ኮሙዩኒኬሽን የሥራ ሂደት አሥተባባሪ እሸቱ ሽፈራው በሰሜን ሽዋ ዞን ባለፉት ጊዜያት የግብር አሠባሠቡ ችግር ገጥሞት ስለነበር ግብር ሠብሥቦ ልማት ለማልማት ፈተና ኾኖ መቆየቱን ነው የነገሩን፡፡ አኹን ላይ ግን ከአንድ ወረዳ በስተቀር ሁሉም አካባቢዎች በመንግሥት ቁጥጥር ስር በመኾናቸው ግብር ለመሠብሠብ ምቹ ኹኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡
ግብር ከሌለ በዞኑ እየተገነቡ ያሉ የልማት ሥራዎች እንደሚቆሙ በመገንዘብ ከባለሙያ እስከ መሪዎች ተቀናጅቶ ዞኑን በአራት ክላስተር በመክፈል ግብር ለመሠብሠብ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ነው የነገሩን፡፡ የሥራ ሂደት አሥተባባሪው በዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች በራሳቸው ገቢ የሚተዳደሩ በመኾናቸው ገቢ በሚገባ ካልሠበሠቡ አጠቃላይ ሥራቸው የሚቆም በመኾኑ ግብር ወሳኝ እንደኾነ ተገንዝበው በትኩረት መሠብሠብ ያለበትን ግብር እየሠበሠቡ ስለመኾናቸውም ነው ያስረዱት፡፡
የግብር ከፋዩ ግንዛቤ እንዲያድግ አስፈላጊ የሚባሉ ሥራዎች እና የቅስቀሳ ሥራ ስለመሠራቱ የተናገሩት አሥተባባሪው በዞኑ ንቃተ ሕሊናው ያደገ ማኅበረሰብ መፍጠር ስለመቻሉ ነው የነገሩን፡፡ በተሠራው ሥራም በተያዘው የሩብ ዓመት ላይ መሠብሠብ ካለበት 33 በመቶ ግብር ውስጥ 31 በመቶ ግብር ስለመሠብሠቡ ነው ያብራሩት፡፡
በገንዘብ ደረጃ 1 ቢሊዮን 13 ሚሊዮን 499 ሺህ 222 ብር መሠብሠቡን ነው ያስረዱት፡፡ ግብሩ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ እንዳሳየም ነው የሚገልጹት፡፡ ከገቢ አኳያ እንደዞን የተሻለ አፈጻጸም ያመጡ ወረዳዎች የበለጠ እንዲበረታቱ እና የበለጠ ገቢ እንዲሠበሥቡ ዕውቅና እና ሽልማት ስለመስጠታቸውም አብራርተዋል፡፡
በዓመቱ እንደ ዞን 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሠብሠብ መታቀዱን የተናገሩት የሂደት አሥተባባሪው አኹን ላይ የተሻለ አፈጻጸም እንዳለም ነው ያብራሩት፡፡ የግብር ትምህርት እና ኮሙዩኒኬሽን የሥራ ሂደት አሥተባባሪው እሸቱ ሽፈራው እንደነገሩን በዞኑ የተሠበሠበው ግብር እስከ 50 የሚደርስ ትምህርት ቤት መገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
ግብርን በተገቢው መንገድ መሠብሠብ ከተቻለ በዞኑ የተጀመሩ የመንገድ፣ የጤና እና የትምህርት መሠረተ ልማቶችን መገንባት የሚያስችል በመኾኑ ሁሉም ግብር መሠብሠብ ላይ ትኩረት እንዲሠጥ አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!