ንጋት ኮርፖሬት የኅብረተሰብ አገልጋይነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።

51

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የንጋት ኮርፖሬትን የሥራ አፈጻጸምን ግምግሟል። የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅት የኾነው ንጋት ኮርፖሬት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በዋና ሥራ አስፈጻሚው አምላኩ አስረስ (ዶ.ር) ቀርቧል።

በውይይቱ በተሰጡ አስተያየቶች ኮርፖሬቱ በሰላም ችግርም ውስጥ ኾኖ ትርፉን ለማሳደግ ያደረገው ጥረት አበረታች ነው ተብሏል። ግብዓት ለአርሶ አደር በማቅረብ አግዟልም ተብሏል። ችግር ላይ የነበሩ ድርጅቶች ወደ አትራፊነት በመመሱ ተበረታትቷል። ንግድ ላይ ያተኮረ ትርፍ ብቻ ሳይኾን አርሶ አደሩን ለሚያሳትፍ አምራችነት እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ትኩረት እንዲሰጥም ተጠቁሟል።

የገበያ ጉድለትን በመሙላት በኩል ካለው ሰፊ የኑሮ ውድነት እና የገበያ ጉድለት አኳያ የበለጠ መሥራት እንዲችል፣ የኮንትራት እርሻ ለአርሶ አደሩ ካለው ጠቀሜታ አኳያ አይቶ አጠናክሮ እንዲቀጥልበት፣ የክልሉን ጥሬ እቃ ታሳቢ ያደረገ ንግድ ውስጥ እንዲገባ እና የኢንዱስትሪ እና የግብርና ትስስርን በማጠናከር ሽግግሩን እንዲያሳልጥ ተጠይቋል።

የሥራ እድል ፈጠራው አነስተኛነት፣ በቀረበው ሪፖርትም ውጤቱን እንጂ ከእቅዱ ጋር ተነጻጽሮ እንዳልቀረበ ተጠቅሶ በቀጣይ እንዲስተካከል ተብሏል። ዶክተር አምላኩ አስረስ ለተነሱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ኮርፖሬቱ የገበያ ጉድለትን በመሙላት በኩል ባለፉት አራት ዓመታት በነበሩ ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያክል አለመሥራቱን ገልጸዋል፤ በቀጣይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ከአንድ ኩባንያ በስተቀር ሌሎቹ ኩባንያዎች በጸጥታ ችግርም ውስጥ ኾነው ትርፋማ መኾናቸውን ገልጸዋል። ግንባታቸው የተጓተቱት የደብረ ማርቆስ የምግብ ኮምፕሌክስ እና የዱቄት ፋብሪካው ያጋጠመውን ችግር ቀርፎ ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ኮርፖሬቱ በማኅበራዊ ልማት መስክ የሚጠበቀውን ያህል አለመሥራቱን የገለጹት ዶክተር አምላኩ በአምሥት ዓመት ስትራቴጅ ችግሮችን ፈትተን በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጡትን አንዳንድ አቅጣጫዎች በሚቀጥሉት የሥትራቴጅክ እቅዶች የተካተቱ እና የሚሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሀናን አብዱ በሰጡት ማጠቃለያ ሃሳብ ኮርፖሬቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2023/24 በሠራቸው ሥራዎች ላይ የተደረገውን ክትትል አቅርበዋል።

የጸጥታ ችግሩን ተቋቁሞ በመሥራት በ2023 የእቅዱን 69 በመቶ ማሳካቱን፣ ገቢውን በማሳደግ እና የተጣራ ትርፉ በተከታታይ ዓመት መጨመሩን፣ ከሚያሥተዳድራቸው ኩባንያዎች ውስጥ የከሠረው አንድ ብቻ መኾኑ፣ ሕጋዊ እና ጤናማ የንግድ ሥርዓት በመከተል ተሸላሚ ኩባንያዎች መኖራቸው፣ ስትራቴጅያዊ ኢንቨስትመንቶች እና ጠንካራ የፋይናንስ መሠረቶች መኖራቸው የኮርፖሬቱ ጥንካሬዎች መኾናቸውን አንስተዋል።

የፍትሐብሔር ክርክር ያለባቸውን ኩባንያዎች የተፈታበት መንገድ፣ ገቢን ለማሳደግ ኩባንያዎችን ለይቶ በትኩረት መሠራቱ፣ ከኤክስፖርት የውጪ ምንዛሪ መገኘቱ፣ ከባንኮች ጋር ባለው መልካም ግንኙነት የውጪ ምንዛሪ ብድር ማግኘቱም ሌላኛው ጥንካሬ እንደኾነ ገልጸዋል። ኩባንያዎች ግልጽ የስትራቴጅ አቅጣጫ ኖሯቸው ከሌሎች ሴክተሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማሳደግ እና የአሠራር ሥርዓት በማበጀት የሠራተኛ ተሳትፎን ማሳደግ ትኩረት እንዲሰጠው ወይዘሮ ሀናን አሳስበዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ ማዳበሪያን ለአርሶ አደር ማድረስን፣ ጤና እና ትምህርት ላይም ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል። የደብረማርቆስ የምግብ ኮምፕሌክስ ፋብሪካ ተጠናቆ ሥራ እንዲጀምር፣ የሕዝብ ግንኙነቱን ሥራ ውስንነት እንዲቀረፍ፣ አርሶ አደሩ በሚፈልገው ልክ የኑሮ ውድነትን እና የገበያ ማረጋጋትን ኅብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ በመሥራት በኩል የታዩ ውስንነቶች ታርመው እንዲሠሩ አሳስበዋል።

ወይዘሮ ሀናን የሕዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አዳጊ ሥራዎች መሥራት እንደሚጠበቅበት እና ምክር ቤቱም ለማገዝ ዝግጁ መኾኑን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግብር ከፋዮች ለሚሰጡት አገልግሎት ደረሰኝ የመስጠት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
Next article“ግብር ለመሠብሠብ የተሻለ ኹኔታ አለ” የሰሜን ሽዋ ዞን የገቢዎች መምሪያ