ግብር ከፋዮች ለሚሰጡት አገልግሎት ደረሰኝ የመስጠት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

38

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ካለው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አንጻር ከተማዋን የሚመጥን ግብር እየተሠበሠበ አለመኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ መረጃ ያሳያል። በ2016 በጀት ዓመት የተሠበሠበውን ግብር እንኳ ማንሳት ቢቻል ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የዘለለ አለመኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ሙሉቀን ብርሃኑ ገልጸውልናል።

በከተማ አሥተዳደሩ የሚሠበሠበው ገቢ ዝቅተኛ በመኾኑ ከተማዋን የሚመጥን እና የማኅበረሰቡን የመልማት ፍላጎት በሚያረካ መንገድ መሠረተ ልማት ለመዘርጋት አዳጋች አድርጎታል። የማኅበረሰቡን የመልማት ፍላጎት ለማሟላት ግብርን በተለይም ደግሞ የአገልግሎት ገቢን በአግባቡ ለመሠብሠብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ነው ኀላፊዋ የገለጹት።

በ2017 በጀት ዓመትም በከተማ አሥተዳደሩ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ እየተሠራ እንደሚገኝም በማሳያነት አንስተዋል። እስከ ኅዳር 13/2017 ዓ.ም 750 ሚሊዮን 952 ሺህ 492 ብር መሠብሠብም ተችሏል ብለዋል። ከዕቅዱ አኳያ አሁን ላይ 35 በመቶ መሠብሠብ ቢጠበቅም በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት መሠብሠብ የተቻለው 19 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ነው።

ይሁን እንጅ አሁን ላይ የተረጋጋ ሰላም በመፈጠሩ መሠብሠብ የሚገባውን ግብር ለመሠብሠብ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከተማዋን የሚመጥን የመሠረተ ልማት ለማሟላት ማኅበረሰቡ የተጣለበትን ግብር በወቅቱ የመክፈል ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ የደረሰኝ አቆራረጥ ሥርዓቱ ችግር ያለበት መኾኑን ያነሱት ኀላፊዋ ግብር ከፋዮች ለሚሰጡት አገልግሎት ደረሰኝ የመስጠት፣ ተገልጋዮች ደግሞ ላገኙት አገልግሎት ደረሰኝ የመቀበል ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል። በከተማ አሥተዳደሩ 17 ሺህ 551 ግብር ከፋዮች ይገኛሉ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የእናቶችን እና የወጣቶችን ሞት ከ40 በመቶ በላይ ይቀንሳል።
Next articleንጋት ኮርፖሬት የኅብረተሰብ አገልጋይነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።