
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቤተሰብ ዕቅድ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ16ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ9ኛ፣ በክልሉ ደግሞ ለሁለኛ ጊዜ “ጥራት ያለው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት” በሚል መሪ መልዕክት ተከብሯል። ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም ውይይት ተደርጓል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች፣ የአፍላ ወጣቶች እና የወጣቶች ጤና አገልግሎት ኬዝ ቲም አሥተባባሪ አዲስዘመን ጫኔ እንዳሉት የቤተሰብ ጤንነትን ለመጠበቅ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አስፈላጊ ነው።
የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የእናቶችን፣ የወጣቶችን እና አፍላ ወጣቶችን ሕመም እና ሞት ከ40 በመቶ በላይ የሚቀንስ አሠራር መኾኑን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ባልታቀደ መንገድ በሚፈጸም ግንኙነት በሚፈጠር እርግዝና ምክንያት በዓመት እስከ 50 ሺህ የሚደርስ ውርጃ እንደሚከሰት አንስተዋል።
የሚፈጠረውን ችግር ለመከላከል ደግሞ ዋነኛው መንገድ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንደኾነ ነው የገለጹት። አኹን ላይ በክልሉ ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መንገድ አገልግሎቱ እየተሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች፣ ሕጻናት፣ አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ዳይሬክተር መልሰው ጫንያለው እናቶችን፣ ሕጻናትን፣ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶችን ጤና ለማሻሻል የተለያዩ የጤና አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።
ከእነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ ደግሞ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ዋነኛው ነው። የእናቶችን ህመም እና ሞት ለመቀነስ ከእርግዝና በፊት ጀምሮ በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድ እና ከወሊድ በኋላም ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሠሩ ቆይተዋል። በተሠራው ሥራም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚወልዱ 100 ሺህ እናቶች ይሞቱ የነበረውን 1ሺህ 30 እናቶች በ2019 ወደ 267 እንዲቀንስ ተደርጓል ብለዋል።
ይሁን እንጅ አኹንም ከ100 እናቶች 19 የሚኾኑት አገልግሎቱን እየፈለጉ በተለያዩ ምክንያቶች የማያገኙ መኖራቸውን ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ወጣቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ።
የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በአደጉ ሀገራትም እየተሠራበት መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ ቤተሰብን በዕቅድ ለመመራት፣ የእናቶችን እና የሕጻናትን ጤንነት ለመጠበቅ አማራጭ በመኾኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!