
ባሕር ዳር:ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ለሚገኙ የጸጥታ አካላት በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ሥልጠና እየሰጠ ነው። ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል የሚሠራ ተቋም ነው። ለሦሥት ቀናት በባሕር ዳር ከተማ በሚሰጠው ሥልጠና ላይ የፖሊስ እና የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል።
የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ቡድን መሪ ፊቶል ሊያኮር የሥልጠናው ዋና ዓላማ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ በማሻሻል የፍትሕ ሥርዓትን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል። “በየትኛውም ቦታ እና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢኾንም የሰዎች ሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ አለባቸው” የሚሉት ፊቶል ሊያኮር እየተሰጠ ያለው ሥልጠና የዘርፉን አካላት አቅም በማሳደግ ለፍትሕ መረጋገጥ እንዲሠሩ ለማስቻል ስለመኾኑ አብራርተዋል።
የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ለሰብዓዊ መብቶች መጣስ ተጋላጭ ስለመኾናቸውም ገልጸዋል። በተለይም ሴቶች እና ሕጻናት ለጉዳቱ ሰለባ ስለሚኾኑ የፍትሕ አካላት በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ግንዛቤ በመያዝ አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት። የመብት ጥሰት በሚያጋጥም ጊዜም ለተጎጅዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከጉዳታቸው ፈጥነው እንዲወጡ ማስቻል ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሠልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በሥራ ላይ በመተግበር የዜጎች መብት እንዲጠበቅ ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሥልጠናውን ከባሕር ዳር በተጨማሪ በሌሎችም የክልሉ ከተሞች የመስጠት ሃሳብ እንዳለ ቡድን መሪው ተናግረዋል። ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ሥልጠናው አማራ ክልል ያለበትን ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ተከትሎ የሚከሰቱ የመብት ጥሰቶችን ለማስተካከል የሚረዳ ነው ብለዋል።
ሥልጠናው ለፖሊስ አባላት መሠጠቱ የመብት ጥሰትን እንዲከላከሉ፣ ጥፋተኞችን ሲይዙም መብታቸው በተከበረ መልኩ ለምርመራ እንዲያቀርቡ እና አስፈላጊውን ሁሉ ክብር እንዲሰጡ የበለጠ ግንዛቤ የሚፈጥር እንደኾነ ተናግረዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሴቶች እና ሕጻናት ክፍል ኀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ታጫውት ዘላለም ሥልጠናው ለተግባራዊ ሥራቸው ጠቃሚ መኾኑን ተናግረዋል። በተለይም የሴቶች እና ሕጻናትን መብት ጥሰት ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ አዳዲስ ክሕሎቶችን አግኝተናል ነው ያሉት።
ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት ለተጨማሪ የሥነ ልቦና ጉዳት እንዳይዳረጉ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ ተጨማሪ ግንዛቤ ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል። ሥልጠናው ተጎጅዎች ፍትሕ እንዲያገኙ ለምንሠራው ሥራም ተጨማሪ ግብአት ይኾነናል ብለዋል ምክትል ኢንስፔክተሯ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!