
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 400 ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደርጓል። ድጋፉን ያደረገው በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኀብረት የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ከትራንስፎርሜሽናል ዲስኤብልድ ሜኪንግ ሚኒስትሪ ጋር በመተባበር ነው።
ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። ድጋፍ የተደረገላቸው አቶ ታደሠ አለልኝ “አምስት ቤተሰብ ይዤ በልተን ከምናድርበት ጦም ውለን የምናድርባቸው ቀናት ይበልጣሉ። በተደረገልኝ ድጋፍ ተደስቻለሁ፤ አመሰግናለሁም” ብለዋል።
ሌላኛዋ ድጋፍ የተደረገላቸው እናት እሟኾይ ሻሼ አታላይም ” ሸምቼ እንዳልኖር ገንዘብ የለኝ፤ ሳንቲም ሲገኝ ኑሮው እሳት ኾነ። ተቸግረን ነበር ለሰጡን ፈጣሪ ይስጣቸው” ነው ያሉት። በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጣና ክፍለ ከተማ የማኅበራዊ አደረጃጀት ዘርፍ ባለሙያ ትዕግስት ጌታቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ 122 ወገኖችን ለይተው ለሚመለከተው አካል መስጠታቸውን ተናግረዋል። አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ሕጻናትን ትኩረት እንደተደረገባቸው ነው የገለፁት።
ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት እና ባለሃብቶችም የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናቱን ኀብረት የበጎነት ተግባር እንዲከተሉ ጠይቀዋል። የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ገብሬ አሰፋ በባሕር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 400 ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ድጋፉ የተደረገው ያለልዩነት መኾኑን የተናገሩት ጸሐፊው ወደፊትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል። በክልሉ ባለው የኑሮ ውድነት እና ካለው የሰላም እጦት አኳያ ሕጻናት መጎዳታቸውን ተናግረዋል። የተጎዱትን ወገኖች ለመደገፍ ተግተው እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በጎጃም እና ጎንደር ቀጣናዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል። በቀጣይም ጎንደር ከተማ ላይ 400 ለሚጠጉ ወገኖች ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል።
የትራንስፎርሜሽናል ዲስኤብልድ ሜኪንግ ሚኒስትሪ መንፈሳዊ አገልጋይ ቴዎድሮስ ታዬ ከኀብረቱ ጋር በመቀናጀት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች የፊኖ ዱቄት እና የምግብ ዘይት ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማውጣት በአማራ ክልል በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አገልጋዩ ከነገ ወዲያም በጎንደር ከተማ በተመሳሳይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።
በቀጣይም ድጋፉን አጠናክረው ለመቀጠል ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!