
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ጉባኤ አቶ ሐጂ ኢብሳን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር አድርጎ ሾሟል፡፡
አቶ ሐጂ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ እና ብቃት እንዳላቸው ሹመቱን ያቀረቡት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጄጌ (ዶ.ር) አብራርተዋል፡፡ ምክር ቤቱም የአቶ ሐጂ ኢብሳን ሹመት በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ በጉባኤው የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁን ያቀረቡት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የግል እና የመንግሥት ድርጅቶች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ የተሟላ፣ ግልጽ እና በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት የፋይናንስ አዘገጃጀት እና አቀራረብ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ የወጣ ነው ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት እና የኦዲት ደረጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ በቂ እና የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ማፍራት አስፈላጊ ኾኖ ስለመገኘቱም አብራርተዋል፡፡
ማቋቋሚያ አዋጁ፣ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መመራቱን ከሕዝብ ተዎካዮች ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!