የሰላም እጦት የፈተነው ጥምር ግብርና

44

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ዓሣን ከሩዝ ሰብል ጋር በማቀናጀትም ኾነ ብቻውን በሰው ሰራሽ ኩሬ ማምረት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተለመደ ነው፡፡ ለአርሶ አደሮችም ጠቀም ያለ ገቢ በማስገኘት ላይ ነው፡፡

የዓሣ እና ሩዝ ሰብል ጥምር ልማት 625 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው የሩዝ ቡቃያ ላይ ይከናወናል። እስከ 1 ሺህ የዓሣ ጫጩቶችን በመጨመር ከሩዙ ጋር እንዲያድጉ እና እንዲራቡ ይደረጋል፡፡

በሩዙ ውሃ የሚራቡት ዓሣዎች ጽዳጃቸውም ለሩዙ በማዳበሪያነት ያገለግላል፡፡ አረሙን በመመገብም ያጠፉለታል፡፡ በዚህም የደረሱትን ዓሣዎች በመሸጥ ወይም በመመገብ፤ ጫጩቶቹን ደግሞ በመሸጥ ሁለገብ ጥቅም ያስገኛል፡፡

አቶ አሥራት ታከለ በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የቲዋዛ ቀና ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው፡፡ ከ2014/15 የምርት ዘመን ጀምሮ በባለሙያ እየታገዙ ዓሣን ከሩዝ ጋር ያለማሉ፡፡ ከዓሣ ሽያጭ ብቻ በመጀመሪያው ዓመት 11 ሺ ብር እና በሁለተኛው ዓመትም 12 ሺህ ብር  መሸጣቸውን ይናገራሉ፡፡ በተጓዳኝም ለምግብነት ይጠቀማሉ፡፡

ሌላኛው አርሶ አደር ደስታው አሥራት ጠቀሜታውን አይቼ በግሌ እየሠራሁ በሽያጭም ኾነ ዓሣ በመመገብ መጠቀም ጀምሬያለሁም ብሏል፡፡ ቀጣይም ሙያዊ ድጋፍ በማግኘት ሥራውን በስፋት መሥራት እንደሚፈልግም ተናግሯል፡፡ እንደሱ የሚሠሩ እና ፍላጎት ያላቸው በርካታ መኾናቸውንም ገልጿል፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ ወረዳ እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የዓሣ ሃብት ልማት አሥተዳደር ባለሙያ ሳለው ባየ የዓሣ እና ሩዝ ጥምር ግብርና ልማት በየዓመቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በወረዳቸው በአንድ ምርት ዘመን ከዓሣ ሽያጭ ብቻ እስከ 14 ሺህ ብር ገቢ ያገኘ አርሶ አደር መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ጥቅሙን ተገንዝቦ ለኩሬ መቆፈሪያ ሁለት ሄክታር የወል መሬት የተለየበት ቀበሌም መኖሩን አስረድተዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ብርቄ ጸጋ ዓሣን ከሩዝ ጋርም ኾነ ራሱን አስችሎ በኩሬ ማምረት እየተስፋፋ ነው ብለዋል፡፡ ከሩዝ አምራች አካባቢዎች ውጪ ያሉ ወረዳዎችም በኩሬ በማልማት መመገብም የዓሣ ጫጩት መሸጥም መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የዓሣ ቴክኖሎጂ ባለሙያ አበበ ፈንታሁን ዓሣን ከሩዝ ጋር አቀናጅቶ ማምረት የተጀመረው በ2011/12 የምርት ዘመን መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በደራ፣ ፎገራ እና ሊቦ ከምከም የተጀመረው የጥምር ግብርና ልማት ወደ ጎንደር ዙሪያ ወረዳም መስፋቱን ገልጸዋል፡፡ በተቀናጀ የግብርና ልማቱ የሩዝ ሰብሉ እና ዓሣው በመመጋገብ ውጤታማ ስለሚያደርግ አርሶ አደሮቹ እንደወደዱት ተናግረዋል፡፡

በፎገራ ወረዳ በስምንት አርሶ አደሮች የተጀመረው ዓሣን ከሩዝ ጋር በጥምር የማልማት ሥራ በየዓመቱ እየሰፋ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በየጊዜው በሚደረግ ሙያዊ ድጋፍና በአርሶ አደሮቹ ጥንካሬ በአንድ አርሶ አደር ከዓሣ ሽያጭ እስከ 22 ሺህ ብር ገቢ መገኘቱን ነው አቶ አበበ የጠቀሱት፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በሠራው የግብርና ሥርጸት ሥራ አርሶ አደሩ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየቱን ነው ባለሙያው የገለጹት፡፡

አነስተኛ የውሃ ኩሬ በማዘጋጀት ዓሣን ብቻ አርብቶ መሸጥ እና መመገብ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም መስፋፋቱን ጠቅሰዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ እና በምሥራቅ ጎጃም በእያንዳንዳቸው በዓመት እስከ 100 አርሶ አደሮች በኩሬ ዓሣ ያረባሉ፡፡ በክልሉ በ2015 ዓ.ም 619 አርሶ አደሮች ዓሣን በኩሬ እንዳለሙ ገልጸዋል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ አሥተደደር እና በፎገራ ወረዳም በጓሮ ዙሪያ ዓሣን ማልማት ተለምዷል፡፡ በክልሉ በየዓመቱ 160 ቶን ዓሣ በኩሬ ይለማልም ብለዋል፡፡

ይኹን እንጂ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የዓሣ ልማት በሰላም መደፍረስ ምክንያት እየተደናቀፈ መኾኑን ነው አርሶ አደሮቹ የሚገልጹት፡፡ በ2016/17 ልማቱን ቢጀምሩም የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዳደናቀፈባቸው ገልጸዋል፡፡

በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የዓሣ ጫጩት ለመጨመር፣ ለዓሣዎቹ ምግብ ለመስጠት ፣ የውሃ መጥለቅለቁንም ኾነ ሌሎች ችግሮችን መከታተል አልቻልንም ነው ያሉት፡፡

ወጣት ደስታውም በሰላም ችግሩ ምክንያት እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራትና ባለሙያዎቹን ለማግኘት አለመቻሉን ጠቅሷል፡፡ የዓሣ ርባታውን አስፍቶ ለመሥራት ቢፈልግም ባለሙያዎቹን ለማግኘት ተቸግሯል።

አርሶ አደሮች በቀሰሙት እውቀት በራሳቸው ጥረት አልምተዋል፤ ነገር ግን እንደ ቀድሞው ተገቢ ሙያዊ ድጋፍ ለመሥጠት የጸጥታ ችግሩ እንቅፋት እንደኾነባቸው ነው የዓሣ ባለሙያው አቶ ሳለው የተናገሩት፡፡

ሥራው በጸጥታ ችግሩ ባይደናቀፍ ኖሮ ከዚህ በላይ ማልማት እና መጠቀም ይቻል ነበር ነው ያሉት፡፡

በሰላም ችግሩ ምክንያት እንደልብ ተንቀሳቅሰው መሥራት ያልቻሉት፣ የባለሙያ ድጋፍና የግብዓት አቅርቦት ለማግኘት የተቸገሩት አልሚዎች በውስን ሥራም ቢኾን ዓሣን አልምተው በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡

በውጤቱም ጫጩቶችን ለአርቢዎች፣ ያደጉትን ዓሣዎች ለምግብ ቤቶች የሚሸጡት አርሶ አደሮች ለቤተሰብም እየመገቡ ነው፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
        👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላምን በማስከበር ሂደት ሕዝቡ በንቃት እንዲሳተፍ ተጠየቀ።
Next articleፌዴራል ፖሊስ በአፍሪካ ጠንካራ የፖሊስ ተቋም ለመኾን እየሠራ ነው።