
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሰላም የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው ።
በምክክር መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ሰላም በመንግሥት ፍላጎት እና ጥረት ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም ብለዋል።
ኅብረተሰቡ ለራሱ፣ ለወገኑ እና ለሀገሩ ሲል ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አስገንዝበዋል ።
በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረው ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል የሁሉንም ቤት ያንኳኳና ከፍተኛ ችግር ውስጥ ያካተተ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ካለፈው መማር እና ለሰላም በመትጋት ሁሉም ማኅበረሰብ የሰላሙ ባለቤት መኾን እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል ። ሰላም በመንግሥት ፍላጎትና ጥረት ብቻ የሚረጋገጥ አለመኾኑን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰላምን በማስከበር ሂደቱ ሕዝቡ በንቃት ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ኅብረተሰቡ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመረዳት የሰላም ተባባሪ እንዲኾን በተደጋጋሚ እየተደረጉ የሚገኙ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
በመድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የከተማ አሥተዳደሩ የተለያዪ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
