
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለ19ኛ ጊዜ በሀገር ደረጃ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔር፤ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን የመንገድ ቢሮ መሪዎች እና ሠራተኞች በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል፡፡ በዓሉ “ሀገራዊ መግባባት ለብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በፓናል ውይይት፣ በደም ልገሳ እና በፅዳት ዘመቻ ነው የተከበረው፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) በዓላት ሲከበሩ ከባለፈው ዓመት የተሻለ መፈጻጸም ለማስመዝገብ የሚያስችል ተቋማዊ አቅምን በማሳደግ ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት በመምራት ሕዝብን ከልማቱ ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የልማቱ ትልቅ አቅም እንዲኾን ሁለተናዊ ድጋፍን ማጠናክር እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
ኀላፊው እያንዳንዱ ባለሙያ ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት በመምራት ተቋማዊ ባሕልን በመፍጠር እና በመፍጠን ኀላፊነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ መወጣት እንዳለበት ነው ያብራሩት፡፡ ሠራተኛው በአገልጋይነት እና በጥሩ ሥነ ምግባር ባለው ኀላፊነት ልክ ውጤት የሚያስመዘግብበት በዓል ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የመንገድ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታደሰ ይርዳው የኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ስለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ ለፓናል ውይይቱ የመነሻ ሰነድ አቅርበዋል። ምክትል ኀላፊው ኢትዮጵያ የምትከተለው የፌዴራል ሥርዓት የራሱ መልካም ነገሮች ያሉት ቢኾንም ከአፈፃፀም እና ከግንዛቤ ጉድለቶች የራሱ ችግሮችም እንዳሉበት ነው የተናገሩት።
ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት የክልሉን የመንገድ ሽፋን ወደ 34 ሺህ 572 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ለማድረስ ግብ መቀመጡንም ባቀረቡት ሪፖርት አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ሥራም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ከኅብረተሰቡ ለማሠባሠብ ያቀደ ሲኾን 5 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከፌዴራል፣ ከክልሉ መንግሥት እና ከሌሎች አጋር አካላት ለማሠባሠብ ወደ ተግባር ምዕራፍ ተገብቷል ነው ያሉት።
ቢሮው በክልሉ ሁሉም ዞኖች በዲዛይን፣ በመንገድ ግንባታ፣ በመንገድ ጥገና እና በተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ ከ600 በላይ የሚኾኑ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ በማስገባት ለ50 ሺህ 120 ወጣቶች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ ነው ብለዋል። የበዓሉ ተሳታፊዎች በዓሉን ሲያከብሩ የቢሮውን ዓላማ ዳር ለማድረስ በአገልጋይነት እና በአርበኝነት መንፈስ ለማገልገል እንደሚተጉ ማረጋገጣቸውን ከመንገድ ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!