
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጋራ የተሠሩ ታሪኮቻችን ያኮራሉ፣ ትውልድን ያስተሳስራሉ፣ ሀገርን ያጸናሉ፣ ከዘመን ዘመንም ያሻግራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን የበዙ የጋራ ታሪኮች ሞልቷቸዋል፡፡ በአንድነት ተነስተው በአንድነት ድል የነሱባቸው፣ በአንድነት ተነስተው ዓለምን ያስደነቁባቸው፣ ነጻነታቸውን ያስጠበቁባቸው፣ ሉዓላዊነታቸውን ያስከበሩባቸው አያሌ ታሪኮች አሏቸው፡፡
የአርበኝነት፣ የጀግንነት፣ የአንድነት፣ የነጻነት እና የሉዓላዊነት ታሪኮቻቸው ለጥቁሮች ሁሉ አርዓያ እንዲኾኑ አድርጓቸዋል፡፡ መከታ እና አለኝታ አስብሏቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የተሣሠሩባቸው፣ ለዘመናት በጽናት የቆሙባቸው ታሪኮች አሏቸው፡፡ የተሣሠሩበት ገመድ ጥብቅ፣ ውሉም ረቂቅ የኾነ፡፡ ምሰሶውም ጠንካራ ነው፡፡
በዚህ ጥብቅ እና ረቂቅ ገመዳቸው አያሌ የመከራ ዘመናትን አልፈዋል፤ ሊለያዩዋቸው የመጡትን ሁሉ ድል እየመቱ በአንድነታቸው ጸንተዋል፤ ክብራቸውን ጠብቀው ኖረዋል፡፡ ከውጭም ከውስጥም በአንድነታቸው፣ በክብራቸው እና በግርማቸው የሚመጡባቸውን ሲያሸንፉ ኖረዋል፡፡ ከዓመታት ወዲህ ግን ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከሰላም ይልቅ ጠብን የሚሰብኩ በዝተውባቸው ኢትዮጵያውያን ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ ፈተናዎቹም መከራ አብዝተውባቸዋል፡፡ ይሄም በአንድነት እና በብዝኀነት የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት እና በአንድነት የሚታወቀውን የኢትዮጵያውያን አኗኗር ፈተና ደቅኖበታል፡፡
የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ትስስር እና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ በሚል ርእስ ባሳተመው ጽሑፍ ላይ “በቅይጥ ምንነት ላይ የተመሠረተ ሀገረ መንግሥት አስፈላጊነት” በሚል ርእስ የጻፉት ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ የብሔር አቀንቃኞች ከተነሱ በኋላ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ አደጋ እንደገጠመው ጽፈዋል፡፡ የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊ መንግሥትነት ባሕሪ መሸርሸር፣ በሀገሪቷ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዝምድናቸውን እንዲያፀኑ ሳይኾን በልዩነቶቻቸው ዙሪያ እንዲደራጁ ማድረግ፣ ለዘመናት የተገነቡ ግንኙነቶች እየፈረሱ ሕዝቦች እንዲጠላሉ እና በየቀያቸው እንዲመሽጉ ያደረገ የፖለቲካ ድርጅት የሀገሪቱን ፖለቲካ መቆጣጠሩ ለብዙ ችግር ዳርጓል።
በዚህ ምክንያት ሁሉንም ያገናኙ የነበሩ የአብሮነት ትርክቶች አዲስ በተፈጠሩ ነጣጣይ እና የቁርሾ ትርክቶች ተተክተዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ “የሰው ሀገሩ ምግባሩ” ይባል የነበረው የሰዎችን የትም ተንቀሳቅሶ የመኖር ብሂል ሽረው “መጤ” እና “ተወላጅ” የሚል ታርጋዎችን በመለጠፍ፣ ልዩነቶችን የሕግ ሽፋን በመስጠት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ዜጎች በአንድ አካባቢ የመኖር ዕድላቸው ገደብ ተጣለበት። መሬትን የሚጠቀሙበት በላዩ ላይ የሰፈሩ ግለሰቦች መኾኑ ቀርቶ “የብሔር እና ብሔረሰቦች” አፅመ ርስት ይኾናል በማለት ሀገሯን በሙሉ የጎሳ ደሴቶች አደረጓት። የታደሉ ሀገሮች ጠባብ ከኾነ የዘውግ አወቃቀር ሰፊ ወደኾነ እና ግዙፍ ጉዳዮችን ወደሚያስፈጽመው ሀገረ መንግሥትነት አድገዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው በተፃራሪው ሀገረ መንግሥቱን እያፈረሱ የዘውግ የበላይነትን ማንገሥ ነው ይላሉ፡፡
አንድ ትውልድ ለሚኾን ዘመን ያለማቋረጥ የተሰበከው እንዴት የአንድ ሀገር ዜጎች እንደምንኾን ሳይኾን የነበሩትን ቀጫጭን ትስስሮች በጣጥሰን እንዴት ለየብቻ መቆም እንዳለብን ነበር። ወንድም ወንድሙ ላያ እንዲነሳ ተቀስቅሷል። የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በጋብቻ መተሣሠራቸው በአደባባይ ተነውሯል፡፡ ሕዝቡ አውቆም ኾነ ሳያውቅ የተበደለው በደል ካለ ይቅር እንዲባባል ሳይኾን የሚገፋፋው ለበቀል እንዲነሳ ነው። “መጤ” እና “ተወላጅ” የሚሉ መለያ ቅፅሎች ዓላማቸው ክፍፍሉን ዘላለማዊ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡
የታሪክ ምሁሩ እንደሚሉት ታሪክ እስካሁን ያረጋገጠው ሐቅ ቢኖር ለፀና እና የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይዎት መሠረቱ የሀገረ መንግሥት ማቋቋም ነው። ከዚህ ጋር አብሮ ልብ ልንለው የሚገባ ሐቅ ሀገረ መንግሥትነት በድንገት እና በአንድ አጋጣሚ ወቅት የሚፈጠር ክስተት ሳይኾን ብዙ ልፋት እና ብዙ ዋጋ የሚጠይቅ ውጤት ነው። አሁን ተሳካላቸው የምንላቸው ሀገረ መንግሥቶች በዚህ ሂደት የተፈጠሩ ናቸው። እንዲህ ባለ ጥረት የተገነባውን ሀገረ መንግሥት ንዶ ሌሎች ተፎካካሪ የዘውግ መንግሥቶችን ለመመሥረት መሯሯጥ ስቃዩን እንደገና መመለስ ይኾናል።
የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥትነት ከጊዜው ጋር እንዲስማማ፣ ለአብዛኛዎቹ ዜጎች የበዛ እርካታ መስጠት እንዲችል፣ ቀጣይ እና ትርጉም ያለው ለውጥ ማካሄድ ያስፈልገዋል ነው የሚሉት የታሪክ ምሁሩ። የትውልዱ ፍላጎት በተለወጠ ቁጥር፣ ዘመኑም አዳዲስ ተግዳሮቶች ይዞ ሲመጣ ሀገረ መንግሥቱ አዲሶቹን ፍላጎቶች የሚያስተናግድበት መዋቅራዊ ስልት እንዲኖረው ያሻል። በተለያየ የታሪክ ወቅት ዛሬ እኛን እንደገጠመን አይነት የማንነትን ጥያቄ የተጋፈጡ ሀገሮች ነበሩ የሚሉት ምሁሩ እነሱ ይህን ጥያቄ ያስተናገዱበትን ስልት ብናጤነው ጠቃሚ ትምህርት እናገኝበታለን ይላሉ። ሀገረ መንግሥቱ በምን መንገድ ይመሥረት? ሀገሩስ የማን ነው? በመካከላችንስ ምን አይነት ዝምድና አለ? የሚሉ ጥያቄዎች ካናወጧት ሀገሮች መካክል አንዷ አሜሪካ ነበረች። ይህ ጥያቄ ሲብላላ ቆይቶ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ደም አፋሳሽ ወደ ኾነ ግጭት መርቷቸው ነበር ነው የሚሉት፡፡
በመጨረሻም ከቀረቡት ክርክሮች መካከል ለብዙዎቹ አርኪ መስሎ የታየው እና በተሻለ ስብዕና ላይ የተመሠረተው ሃሳብ “አሜሪካ የዚህ ዘር፣ ወይም የዚያ ዘር ሀገር ሳትኾን ከየትም ይመንጩ፣ ከየትም ይምጡ አሁን ምድሯ ላይ የሚኖሩት የቅይጥ ሕዝቦች ሀገር ናት” የሚለው ነበር። ይህ ቅይጥ ማንነት ሰውን በሰውነቱ እንጂ በዘሩ ወይም በዘውጉ ምንነት የማይመዝን፣ ሰዎች ራሳቸውን የሚገልጹት ከሌላው በሚለያቸው ማንነት ሳይኾን ከሌላው ጋር በሚያዛምዳቸው የጋራ ግንኙነት እና የጋራ ጥቅም ይኾናል። ሁሉም የሚጋሯቸው የጋራ ጥቅሞች ደግሞ እንደ ነፃነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነት ያሉ እሴቶች ናቸው ነው የሚሉት፡፡ ለዚህ ዝምድና መጥበቅ ዋስትናዎች ናቸው። በእነዚህ እሴቶች ላይ የተመሠረተ ዜግነት ይበልጥ አቃፊ፣ ይበልጥ ሰብዓዊ ነው ይላሉ፡፡
በአንፃሩ ጠባብ ማንነት ላይ ሀገረ መንግሥቱን እንመሠርታለን የሚሉ ኀይሎች የሚሠባሠቡት ሌሎችን በማግለል፣ ከሌላ ዘውግ አባላት ጋር አለን በሚሉት ልዩነት ላይ ያተኮረ በመኾኑ ሕዝቦችን እርስ በእርስ የሚያናክስ፣ የዘር መድሎን የሚያበረታታ እና ለግፍ እና ለሰቆቃ እርምጃዎች በር የሚከፍት ነው ይላሉ የታሪክ ምሁሩ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት በተናጠል የዘውግ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥብሥብ በተፈጥሮው በሌሎች ኪሳራ ራሱን ማጎልበት ላይ የሚያተኩር በመኾኑ ለሁሉም ስጋት ከመኾን አያልፍም። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ገና ሀገረ መንግሥትነቱ ሲጠነሰስ ጀምሮ በቅይጥ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በመኾኑ አሁን ከብዙ ዘመናት በኋላ ፍች እንፈጽም፣ የተቀላቀለውን እንለያየው እና ነጠላ ማንነት ይንገሥ ከተባለ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ እና ጥፋት ለመገመት አያስቸግርም ነው የሚሉት። ኢትዮጵያን ከቀውስ ለመታደግ በቅይጥ ማንነት ላይ የተመሠረተ ሀገረ መንግሥትነትን የሚያጐለብት ተሐድሶ ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለው ጽፈዋል ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም ከተናጠል ይልቅ የጋራ እና ገዥ ትርክቶችን መፍጠር ለተሳካ ሀገረ መንግሥት ግንባታ አስፈላጊ ነው ብሎ ገዢ ትርክቶችን የማጉላት ሥራ እየሠራ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚኮሩባቸውን የአንድነት እና የአርበኝነት ታሪኮቻቸውን ማጉላት ደግሞ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ነጠላ ወይም የተናጠል የሚባሉ ትርክቶች ከገዢ ትርክቶች ልቀው መግነን ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ኪሳራን እንጂ ትርፍን አልሰጧትምና፡፡ ገዢ ትርክት ይገንባና ይጉላ ሲባል ግን የግለሰቦችን ማንነት እና ምንነት ይደፈጥጣል ማለት ግን አይደለም፡፡
የታሪክ እና የባሕል ምሁሩ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ በትናንቱ ትርክቶች እየተማርን፣ ድክመት እና ጥንካሬዎችን እየለየን፣ አዲስ የጋራ ታሪኮችን መሥራት አለብን ይላሉ፡፡ አባትህ አንተን አይደሉም፣ አንተም አባትህን አይደለህም፣ ከአባትህ ግን መማር ትችላለህ፣ ከእርሱ እየተማርክ የጋራ የኾነ ነገር መሥራት ይቻላል ነው የሚሉት፡፡ በትናንትና መማር እንጂ በትናንትና መኖር አይቻልም ነው ያሉት፡፡ እኛ ባልሠራነው መሳሪያ ከምንገዳደል በቆዬው ባሕል እና እሴታችን አንድ ኾነን ለአንድነት መሥራት አለብን ይላሉ፡፡ ሀገርን ከጠላት መከላከል እንጂ እርስ በእርስ መገዳደል ጀግንነት አይደለም ነው የሚሉት፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ነባራዊ ሁኔታን በመረዳት ለጋራ መፍትሔ በጋራ መምከር ይገባልም ይላሉ፡፡
ለጋራ ሀገር የጋራ ታሪኮችን ማጉላት፣ የጋራ ታሪኮችንም መሥራት እና መጠበቅ የተገባ ነው፡፡ የጋራ ታሪክ ያኮራል ያሻግራልና፡፡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ስሪትም የጋራ፣ በጋራ ለጋራ የኾነ ነው፡፡ ይሄን ማስቀጠል እና ማጽናት ደግሞ ሀገርን ያጸናል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!