
አዲስ አበባ: ኅዳር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ስንዴን በስፋት እና በጥራት ከሚያመርቱ የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል ኦሮሚያ ክልል አንዱ ነው። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በኦሮሚያ ክልል ባሌ እና አርሲ ዞኖች ተገኝቶ የመኸር ወቅት የሰብል ልማት እንቅስቃሴን ተመልክቷል። በአርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር አቡ በልፋ በአራት ሄክታር ማሳ ላይ ያለሙትን የስንዴ ሰብል በዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ኮንባይነር ሲሰበስቡ ነው ያገኘናቸው።
ካለሙት መሬትም ከ200 ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት እንደሚጠብቁ ለአሚኮ ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስንዴን በኩታ ገጠም በማልማት ከራሳቸው የምግብ ፍጆታ ባለፈ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። ስንዴ የምናመርተው ለራስ የምግብ ፍጆታነት እንዲውል ብቻ ሳይኾን ለውጭ ሀገር ኤክስፖርት ለማድረግ ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ የራሳችንን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት ያስችላል ነው ያሉት።
በዚሁ ወረዳ ሰብላቸውን በኮምባይነር ሲሰበስቡ ያገኘናቸው ሌላኛው አርሶ አደር ቱኔ ሮባ በምርት ዘመኑ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ማልማታቸውን ነግረውናል። ከለማው መሬትም እስከ 150 ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠብቁ ነው የነገሩን። ባለፉት ዓመታት በሄክታር ከ20 እስከ 30 ኩንታል ምርት ሲያገኙ እንደነበር የጠቀሱት አርሶ አደሮቹ አሁን ላይ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀማቸው ምርት መጨመሩን ተናግረዋል። በሄክታር በአማካይ ከ50 እሰከ 60 ኩንታል እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በሄጦሳ ወረዳ 36 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ብቻ መልማቱን የወረዳው ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኑሩ ሁሴን ተናግረዋል። ከዚህም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ብለዋል። ምርቱ ከምግብ ፍጆታ ባለፈ 50 በመቶው ለዱቄት ፋብሪካዎች እና ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብም ተናግረዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ድኤታ ከበደ ዴሲሳ ሀገሪቱ አሁን ላይ ከውጭ ስታስገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ በብዛት እና በጥራት በማምረት ከሀገር የምግብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ እያቀረበች ነው ብለዋል። በዘርፉ የተሠማሩ አርሶ አደሮች የእርሻ ትራክተር፣ የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነር፣ የአፈር ማዳበሪያን በአግባቡ በመጠቀም እና በኩታ ገጠም በማልማታቸው ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ሚኒስቴር ድኤታው አንስተዋል።
የግብርና ግብዓቶች ወደ ሀገር ውስጥ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መደረጉ ዘመናዊ ግብርና እንዲስፋፋ፣ ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!