
አዲስ አበባ: ኅዳር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ የሰላም፣ የብልጽግና እና የልማት ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ነው በጉባኤው ከ22 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮች እና ሚኒስትሮች ተገኝተዋል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዮ አጽቀስላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ተገኝተዋል። የተመድ እና አህጉራዊ እንዲሁም ቀጣናዊ ተቋማት ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ አፍሪካ የጂኦ ፖለቲካል እና ጂኦ ኢኮኖሚ ፍክክር በአፍሪካ እና በቀጣናው በኃይል እየተጫነን ነው ብለዋል። ይህንን በመረዳት በአግባቡ መቆጣጠር እና ማሥተዳደር ካልተቻለ ሰላምን ለማምጣት ያስቸግራል ብለዋል። በአሁኑ ጊዜ ያለውን የቴክኖሎጅ አቅም እና የዓለም ሥርዓት ተረድቶ መሥራት አፍሪካዊ ዕድገት ለማስመዝገብ እንደሚረዳም አስገንዝበዋል።
አፍሪካን ለሰላም እና ልማት የምትሠራ አህጉር ትሁን ከተባለ አጀንዳ 2063 ላይ የተቀመጠውን የሰላም እና ዕድገት መሠረት በማድረግ መሥራት እንደሚገባም ነው ያብራሩት። የወጣቶች እና የሴቶችን አቅም ትኩረት አድርጎ ማሳደግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት። ለዚህም እንደአ ፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ያሉ አቅማቸውን ማሳደግ የሚያስችሉ ጠቃሚ ሁነቶች ላይ መሥራት አስፈላጊ መኾኑንም ነው ያብራሩት።
በዕውቀት እና ተቋም ላይ መሠረት ያደረገ ሥራ፣ አካታች እና ሁሉን አቀፍ እሳቤዎች፣ ቴክኖሎጅዎች እና የዓለምን ሥርዓት የተገነዘበ አሠራርን መከተል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ያለን የሰው ኀይል በአግባቡ ተረድቶ እና ይዞ ለልማት እና ለሰላም መጠቀም ይገባልም ብለዋል። ይህ ኮንፈረንስም አፍሪካ ሰላም እና ልማት ለማምጣት ለምታደርገው ጥርት አቀጣጣይ አቅም ኾኖ ያገለግላል ነው ያሉት።
የተመድ ዋና ጸሐፊ ረዳት እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ጉዳዮች ዋና አሥተባባሪ ራሚስ አላክባረቭ (ዶ.ር) ለሁሉም አፍሪካ ሰላምን ለማዳርስ የአፍሪካ አጀንዳ 2063 ላይ መሠረት አድርጎ መሥራት ይገባል ብለዋል። ዶክተር ራሚስ ሰላም የለውጥ ሁሉ መሠረት ነው ብለዋል። የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ የሚለው ሃሳብ ጠቃሚ ስለመኾኑም አብራርተዋል። የአህጉሪቱን ባሕላዊ እና ነባር የግጭት መፍቻ መንገዶች እና ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት መፍትሔ በሚያመጣ መንገድ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ይህም ስር የሰደዱ አለመግባባቶች ላይ መፍትሔ ለመስጠት ይጠቅማል ነው ያሉት።
የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በኢትዮጵያ አፍሪካዊ ችግሮችን አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት በሚል የተሠራው ሥራ በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት እና በሌሎች እገዛ የተጀመረው ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ኑሮ የመመለስ እና ትጥቅን የማስወረድ ሂደት ለዚህ ሁነኛ እና ቆራጥ ውሳኔ ኾኖ በተምሳሌትነት የሚቀርብ እንደኾነም አስረድተዋል።
አህጉራዊ ሰላም እና ዕድገት ይምጣ ሲባል በጋራ በመኾን ያለድንበር በመተባበር ሲሠራ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ይህም ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ አህጉር ለማስረከብ እንደሚረዳም ነው ያብራሩት። በአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች የሰላም እና ደኅንነት ኮምሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዴየ ሰላም፣ ብልጽግና እና አካታች ኢኮኖሚን መገንባት ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካን የሰላም ሽግግር ለመገንባት ለሚደረገው ሂደት ኮንፈረንሱ ጠቃሚ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ሰላም የሚረጋገጠው በጋራ በሚደረገው ጥረት እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ አንዷለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!