መልካም እሴቶቻችንን በመጠበቅ የሀገርን ክብር ከፍ ማድረግ ይገባል።

31

ሰቆጣ: ኅዳር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቀደምት አባቶቻችን ልዩነቶችን በምክክር፣ ጥልን በይቅርታ፣ ደም መቃባትን በሽምግልና ሥርዓት እየፈቱ ኢትዮጵያን ጠብቀው አቆይተዋል። እነዚህ መልካም እሴቶቻችን በመሸርሸራቸው ምክንያት የከበረው ሽምግልና ከክብሩ ዝቅ እያለ፣ ጦርነት የችግር መፍቻ እየመሰለ መጥቷል።

ጦርነት ውድመት የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ከነየመን፣ ሊቢያ እና ከጎረቤት ሱዳን መረዳት ይቻላል። ቀረብ ሲልም በራሳችን ካሳለፍነው ከሰሜኑ ጦርነት እንደሀገር የደረሰውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ መመልከት ይቻላል። ወጣት ሙሉቀን ታድጎ ቀደምት አባቶቻችን ያቆዩትን መከባበር፣ መደጋገፍ እና አብሮነታችንን የሸረሸረው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያደረሰው ተጽዕኖ ነው ብሏል።

“አብሮህ ያለው ጓደኛህ ካንተ ይልቅ ልቡን ለስልኩ ይሰጣል” የሚለው ወጣቱ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ግጭት አባባሽ ድርጊቶች ወጣቱን እየበረዙት ነው ብሏል። ወጣት ዘውድ አወጣ ታላላቆችን ማክበር እና የተቸገሩትን የመርዳት እሴቶች እየተዳከሙ መምጣታቸውን ትናገራለች። ቀደምት እሴቶቻችንን ለመመለስ የበጎ አድራጎት ማኅበራትን ማስፋፋት እና የሃይማኖት አባቶችን ምክር መቀበል ከወጣቱ ይጠበቃል ትላለች።

ወጣት ሰሎሞን ደሳለኝ መንግሥት ወጣቱ በሱስ እና በጎጂ ልማዶች መጠመዱ መልካም እሴቶቻችንን በመርሳት ክፋትን እንደ ተራ ነገር እንድንለማመድ አድርጎታል ብሏል። የሱስ ቦታዎችን በመዝጋትና ለወጣቱ የሥራ ዕድል ከፈጠረ ችግሮች ይፈታሉ ብሎ እንደሚያምን ነው የገለጸው። በሰቆጣ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሥነ ምግባርና ግብረገብ ትምህርት አሠልጣኝ መምህር አበበ አይናለም እሴት ማለት ማኅበረሰቡ ለዘመናት ጠብቆ ያቆያቸው በትውልድ ቅብብሎሽ የመጡ ችግር ፈች፣ አቀራራቢና አብሮነትን የሚያጎለብቱ ልምዶች ናቸው ብለዋል።

ከመልካም እሴቶቻችን መካከልም ጥቂቶቹ ቃልን ማክበር፣ እርቀ ሰላም፣ መደጋገፍ፣ አብሮነትና ሌሎችም ይጠቀሳሉ ብለዋል መምህር አበበ። እነዚህን መልካም እሴቶቻችንን ለመመለስ በሥርዓተ ትምህርት በማካተት ህጻናትን በምግባር መቅረጽና በወጣቱ ሥነ ልቦና ላይ በመሥራት እሴቶቻችንን መመለስ እንችላለን ነው ያሉት።

የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ሰቆጣ ከተማ ሰላም ወዳድ የኾኑ ወጣቶች መኖሪያ ናት፤ አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላምም የሚበረታታ ነው ብለዋል። እንደ ክልልም ኾነ እንደ ሀገር ከገባንበት የሰላም እጦት ለመውጣት ቀደምት መልካም እሴቶቻችንን መመለስና መተግበር አለብን ነው ያሉት።

መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ መስጠቱ አበረታች ነው የሚሉት ከንቲባው አባቶቻችን ያቆዩትን እርቀ ሰላም በመጠቀም ታጣቂ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል። ከጦርነት የሚገኝ ጥቅም አለመኖሩን በመረዳት ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት እየታየ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም መመለስ እንደሚገባም አቶ ጌትነት ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም አቀፍ የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀን ለ16 ቀናት በሁሉም ከተሞች እንደሚከበር የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleአፍሪካ ሰላሟን ለማረጋገጥ የዓለምን አሰላለፍ የተረዳ የጂኦ ፖለቲካ ፍክከርን በአግባቡ ማሥተዳደር እንደሚገባት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀስላሴ ተናገሩ፡፡