
አዲስ አበባ: ኅዳር 16/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀን በዓለም ለ33ተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ ከኅዳር 16 እስከ ታሕሳስ 01/2017 ዓ.ም በሁሉም ከተሞች እንደሚከበር የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ዓለም አቀፍ የነጭ ሪቫን ቀን ወይም 16 ቱ የፀረ- ጾታዊ ጥቃት ቀን ንቅናቄ በተለያዮ ሴቶችን ከጥቃት ለመታደግ በሚረዱ ተግባራት ላይ በመመሥረት በየዓመቱ ይከበራል።
የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ንቅናቄ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር በጋራ በመኾን በድሬዳዋ ከተማ ተጀምሯል። በፕሮግራሙ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)፣ የድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀሪቡ ቡዕዝ እና የክልል የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኅላፊዎች ተገኝተዋል።
በንቅናቄው “የሴቷ ጥቃት የእኔም ነው ዝም አልልም” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዮ መርሐ ግብሮች ተከናውኗል። በንቅናቄ ቀናቱም የሴቶች ጥቃት አስከፊነት ዙሪያ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ድርጊቱን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። መንግሥት ጾታዊ ጥቃት ከግለሰብ ጀምሮ በማኅበረሰብ እና በሀገር ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሴቶች እና ሕጻናት ሰብዓዊ መብት መከበር ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብሎ በማጽደቅ በሥራ ላይ መኾኑን ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
የሴቶች ጉዳይ የመሥሪያ ቤቱ ኀላፊነት ብቻ አለመኾኑንም ገልጸዋል። ሴቷ ጥቃት ከደረሰባት በኋላም ተገቢውን የኾነ የጤና እና የሥነ ልቦና ጉዳት ማገገሚያ ተቋማት እንድታገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን እየሠራን ነው ብለዋል። በቀጣይም ሁሉም የሴቷ ጥቃት የእኔ ነው በማለት ሴቷ ጥቃት እንዳይደርስባት፤ ከደረሰባትም ጥቃት አድራሾች ተገቢውን እርምጃ እንዲያገኙ ትብብር ያድርግ ነው ያሉት።
19ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀን ለ16 ቀናት በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች በተለያዮ ንቅናቄዎች ይከበራል።
ዘጋቢ: ራሔል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!