
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፀረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ “የሴት ልጅ ጥቃት የኔም ነው ዝም አልልም” በሚል መሪ መልዕክት ምክክር እየተካሄደ ነው።
ፋና አዲስ ትውልድ ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ያልኾነ ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት የ16 ቀናት የፀረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ ወርክሾፕ ከክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ነው በባሕርዳር እያካሄደ የሚገኘው፡፡
መድረኩ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራን ለማሳደግ፣ አካል ጉዳተኞች ላይ ማኅበረሰቡ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ የመስበር እና ድጋፍ የማድረግ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የ16 ቀናት የፀረ ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ መርሐ ግብር የሴቶችን ጥቃቶች ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኀላፊዋ የሴቶችን ጥቃት ከመከላከል ባለፈ የጉዳቱ ሰለባዎች አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ የመደገፍ ሥራ በዘመቻው እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ቢሮው በእነዚህ ቀናቶች ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል በልዩ ትኩረት እየሠራ ስለመኾኑ ነው ያስገነዘቡት፡፡
በሴቶች ላይ የሚታየው ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን የገለጹት ኀላፊዋ ሴቶችን ከጉዳት ለመከላከል እየተሠራ መኾኑን ነው ያብራሩት፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ ኀላፊችን ጨምሮ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች የሃይማኖት አባቶች እና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣቱ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!