“በአንድነት እንኑር፤ በፍቅር እንሻገር”

83

“በአንድነት እንኑር፤ በፍቅር እንሻገር”

ጎንደር: ኅዳር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድነት የኖሩት ገናና ታሪክ ሠርተዋል፤ በአንድነት የኖሩት ፈተናን ሁሉ በድል አልፈዋል፤ በአንድነት የኖሩት አያሌ የሥልጣኔ ታሪኮችን ጽፈዋል፤ በጠላቶቻቸው ላይ ሠልጥነዋል፡፡

 

ሀገርን ከእነድንብሩ፣ ነጻነትን ከእነክብሩ ለልጅ ልጅ አቆይተዋል፡፡ የታላቅ ሀገር ልጆች የተባሉት በአንድነት የኖሩት፣ በፍቅር የሚተሳሰሩት፣ በኅብረት የሚያምኑት፣ ልዩነትን እንደ ጌጥ የሚጠቀሙት፣ በአንድነትም እንደ ሸማ የሚለብሱት፣ ጥበበኛ ሴት እንደሰፋቻት መሶበወርቅ ልዩነትን እንደ ኅብረ ቀለማት የሚጠቀሙበት ናቸው፡፡

 

ፍቅር መከራን ያሳልፋልና በፍቅር ተሻገሩ፤ ፍቅር ከፍ ከፍ ያደርጋልና ለፍቅር በፍቅር ኑሩ፡፡ በፍቅር የተገነባች ሀገር መሠረቷን ነፋስ አይገፋውም፤ ጠላት ገፍቶ አይጥለውም፡፡ በፍቅር የተሠራች ሀገር መሰሶዋ ብርቱ ነው፤ ማገሯም ረቂቅ ነው፤ ጣሪያውም እጹብ ድንቅ የሚያሰኝ ነው፤ ቅጽሯም ያማረ እና የተዋበ ነው፡፡

 

ብርቱዎች ለሀገር ኖረዋል፤ ለሀገር አልፈዋል፤ ለትውልድ የመሥዋዕት በግ ኾነዋል። ለነጻነት ሁሉን ነገራቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፤ ለሉዓላዊነት መራራ ጽዋን ተጎንጭተዋል። ለከበረች ሠንደቅ ዓላማቸው ድል ብቻ ለምታውቅ ሀገራቸው ሲሉ በእሾህ እና በአሜካላ ተረማምደዋል፣ በሀሩር እና በቸነፈር ተመላልሰዋል፡፡

 

አንድ ኾነው እንደ ዓለት ጠጥረው፣ እንደ ብረት ጠንክረው፣ እንደ ተራራ ገዝፈው፣ እንደ ውቅያኖስ ጠልቀው ሀገርን ከሚተናኮል ጠላት ጠብቀዋል፤ ከሚዳፈር ወራሪ ታድገዋል፡፡ የልጅ ልጅ የሚኮራበት፣ ዓለም አርአያ አደርጎ የሚነሳበት ሥልጣኔን ሠርተዋል፡፡

 

ኢትዮጵያውያን በአንዲት ሀገር፣ ለአንዲት ሀገር በአንድነት ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በሚሉት ብርቱ ገመድ ተሳስረው፤ ኢትዮጵያ በሚሏት ጥንታዊት ቤት ተጠልለው ለዘመናት ጸንተዋል፡፡

 

አንድነት ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን መታወቂያ ክብራቸው፣ የማይወልቅ እና የማያልቅ ካባቸው፣ የማይሰበር በትራቸው፣ መከላከያ ጋሻቸው፣ መውጊያ ጦራቸው፣ መቀመጫ ዙፋናቸው፣ መረማመጃ ጎዳናቸው፣ መኖሪያ ቤታቸው፣ መሸጋገሪያ ድልድያቸው፣ መከበሪያ ዋሳቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ታሪክ ሲነሳ አንድነት ይነሳል፡፡

 

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ትስስር እና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ በሚል ርእስ ባሳተመው ጽሑፍ ረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ በተለያዩ ወጎችና ባሕሎች ተቀርፆ፣ ተገምዶና ተቆራኝቶ የተሠራ የጋራ እሴት ነው። እነዚህም የትስስር እና የመስተጋብር እሴቶች ለኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን የሚያቻችሉበት ምቹ የሆኑ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ፈጥረውላቸዋል።

 

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እና የአሥተዳደር ክፍሎችን የጋራ ቤታቸው አድርገው ሲመለከቱት እና ሲኖሩበት የቆዩ መኾኑን ታሪክ በገሀድ ይመሰክራል። የውህድ ማንነት ያላቸው ሰዎች ለዚህ ታሪካዊ ጉዞ አይነተኛ ማሳያ ናቸው። ስለሆነም ከሳሎን ቤት እስከ አደባባይ ቤተሰባዊና ሀገራዊ ትስስር ሲያጠናክሩ ቆይተዋል ተብሎ ተጽፏል፡፡

 

የታሪክ እና የባሕል ምሁሩ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ኢትዮጵያውያን በነጻነት፣ በሉዓላዊነት እና በክብር እንዲቆዩ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ ተፈጥሮ የሰጣቸው ጸጋ ነው ይላሉ፡፡ ብዙ ጊዜ በተራራ እና በበረሃ የሚኖሩ ሕዝቦች ለጠላት አይደፈሩም፤ አትንኩኝ ባዮች ናቸው፤ ኢትዮጵያም ተራራማ ሀገር ስለኾነች ነዋሪዎቿም የተራራ ሀገር ነዋሪዎች ስለኾኑ አትንኩኝ ባዮች ናቸው ይላሉ፡፡ የተፈጥሮ ሁኔታው ለኢትዮጵያውያን በብዙው ጠቅሟል ነው የሚሉት፡፡

 

በታሪክ ውስጥ የተራራ ሕዝቦችን ማሸነፍ አይቻልም፤ የተራራ ሕዝቦች ነጻነታቸውን ይወዳሉ፤ በነጻነታቸው ላይ አይደራደሩም። ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ነጻነታቸውን አብዝተው የሚወዱ በነጻነታቸው እና በሉዓላዊነታቸው የማይደራደሩ ናቸው፡፡ የውጭ ጠላት አያሸንፋቸውም፤ የተራራ ሕዝቦች ስሜት፣ አመለካከት አትንኩኝ ባይነት፣ ድል አድራጊነት ነው፤ ከዚያም አለፍ ሲል ፍትሕ ፈላጊዎችና እና ፍትሕን የሚነፍግ ሲመጣ የሚገጥሙ ናቸው ነው የሚሉት፡፡

 

ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውን አብዝተው የሚወዱ፣ ፍትሕን የሚያውቁ በመኾናቸው የውጭ ጠላት አሸንፏቸው አያውቅም፡፡ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ተደርገውባቸዋል፤ ነገር ግን ድል አድርጎ ነጻነታቸውን የወሰደባቸው የለም፡፡ የተራራ ሕዝብ እልኸኛነትና ደም መላሽነት ባሕሪ በውስጣቸው ስላለ ለማንም አልተበገሩም ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለውጭ ጠላቶቻቸው አይደፈሬ እና አይነኬም ቢኾኑ በውስጣቸው ግን ግጭቶች ሲካሄዱ ኖሯል ነው የሚሉት፡፡ በየቦታው የሚነሱ ሽፍታዎች ነበሩ፡፡ አሁንም እንደዚያው ቀጥሏል፡፡ ልዩ የሚያደርገው ግን አሁን ላይ ዘመኑ ባመጣው ሚዲያ አማካኝነት በየቦታው የሚፈጸመውን ሁሉ እንሰማለን፤ ይሄን በማስማታችን ደግሞ አዕምሯችን ይረበሻል፡፡ ግጭት ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተለመደ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ መሻገር አለመቻል ደግሞ ሌላ ችግር ነው፡፡

 

በውስጣችን በሚነሱ ግጭቶች እና ችግሮች ምክንያት ታዲያ በሚፈለገው ልክ እንዳናድግ አድርጎናል ነው የሚሉት፡፡ የውጭ ጠላቶቻችን በመለስንበት እና ድል በምንመታበት አግባብ የውስጥ ችግሮቻችን እንዴት መፍታት አለብን በሚለው ጉዳይ ላይ በሚገባ የሠራን አይመስለኝም ይላሉ፡፡

 

ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝም አጼ ምኒልክና ኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያውያን ከውጭ ለሚመጣ ጠላት የማይበገሩ እና የማይገብሩ፣ በነጻነት እና በድል አድራጊነት የኖሩ ኾነው ሳለ በውስጣቸው ግን እስካሁን ድረስ የተሟላ ሰላም እንደሌለ ጽፈዋል፡፡

 

ስለ ውስጣዊ ሰላም ማጣት ሲጽፉም “ካለመስማማታችን የተነሣ ሌሎች ሕዝቦች በአእምሮና በጥበብ እየበረቱ ሲኼዱ እኛ ወደኋላ ቀረን፡፡ የዱሮውም ያኹኑም ኑሮዋችን እጅግ ያሳዝናል። በመላው ዓለም ላይ ሰላም ሲሰፋ አእምሮም ስትበራ እኛ በጨለማ እንኖራለን፡፡

 

እርስ በርሳችን መጠራጠርንም አልተውንም፡፡ ሕዝቦችም ኹሉ እርስ በርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለልማታቸው ባንድነት ኹነው ሲደክሙ እኛ አንድ ዘር እና ወንድማማች መኾናችንን አልተገለጸልንም፡፡ እርስ በርሳችን መፋጀትም እስከዛሬ ድረስ ጀግንነት ይመስለናል” ብለዋል ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፡፡

 

ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግጭት እና ያልተገባ ፉክክር መግራት ያልተቻለ ችግር ነው ይላሉ፡፡ የውርስ እና የሥልጣን ጥያቄዎች ኢትዮጵያን ሰላም እየሰጧት አይደለም ነው የሚሉት፡፡ በታሪክ እንማራለን እንጂ በታሪክ አንኖርም፤ ታሪክ ምንም አልጎዳንም፤ የጎዳን አረዳዳችን ነው፤ ታሪክን እንደ እምነት ከወሰድነው የአሸናፊ እና ተሸናፊ ጉዳይ ይመጣል፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ አንተ ነህ እኛ ነን የሚል ጉዳይ ይፈጠራል፤ ይህ ሲፈጠር ደግሞ አለመግባባት አለ ይላሉ ምሁሩ፡፡

 

በአንድ ታሪክ ውስጥ የአሸናፊነት አመለካከት፣ የተሸናፊነት አመለካከት እና የታዛቢ አመለካከት አለ ይላሉ። ምሁሩ እንደሚሉት ታሪክ፤ እውነት እና ውሸትን አይሠራም፤ አዕምሯችን የሚያጫውት ግንዛቤን የሚያሰፋ ነው እንጂ፡፡ በአንድ ታሪክ ውስጥ የሦስቱንም አመለካከት ካነበብን የተሻለ ግንዛቤ ያለን የተሻሉ ሰዎች እንኾናለን፤ ታሪክ እንደ ዕውቀት ከወስድነው እሰየው፤ ታሪክን እንደ እምነት ከወሰድነው ግን ችግር ነው ይላሉ፡፡

 

በታሪክ መነታረክ ማቆም አለብን፤ በታሪክ አንኖርም፤ ዛሬ ላይ የሚያኖረን ሥርዓት ያለው አካሄድ ነው፤ ጥያቄው ትናንት እንዲህ ነበርኩ ማለቱ ብቻ ሳይኾን ለዛሬ ምን ሠራሁ የሚለው ነው ብለዋል፡፡ አባቴ ትናንት ሃብታም ከነበረ ዛሬ እኔ በድህነት እየኖርኩ አባቴ ሃብታም ነበር ብል ምንም አይጠቅመኝም፤ የሚጠቅመኝ አባቴ እንዴት ብሎ ነው ሃብታም የኾነው የሚለውን መማር ስችል እና ሃብታም እንድኾን ሥሠራ ነው፣ የአባቴን ታሪክ ብቻ ስናገር ብኖር ግን ምንም አይጠቀምኝም ይላሉ፡፡

 

እኛ ለሀገራችን እና ለነጻነታችን ለመሞት ዝግጁዎች ስለኾን ጠላት አያሸንፈንም፡፡ ዓድዋን ኾነ ከዚያ በኋላ እና ከዚያ በፊት ያሉት ታሪኮቻችን በአሸናፊነት የተቋጩት በሀገር ጉዳይ ለሞት የተዘጋጀን ስላለ ነው፡፡ ለነጻነታችን እንደምንተባበረው ሁሉ ለውስጣዊ ችግሮቻችንም መተባበር እና መመካከር አለብን፡፡ የችግሮቻችን ምንጭ ካላደረቅነው ጫፉ ላይ ብናወራ ምንም ነው ይላሉ፡፡

 

እንደ ምሁሩ ገለጻ ኢትዮጵያውያን አሁንም በአንድነት ነው የሚኖሩት፤ ሁሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚኖረው፤ በአንዲት ሀገር የሚኖሩ ዜጎች አንድ ናቸው አይደሉም እያሉ መነታረክ አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን በትናንትና ቁስል የሚብሰለሰለውን፤ ግጭትን የሚያነሳውን በመመካከር ማስተካከል፣ የሰላም እጦት ምንጮችን ማድረቅ ይገባል ብለዋል፡፡

 

ግለሰቦች ላይ ከማተኮር ይልቅ ሥርዓትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን ይላሉ፡፡ ውስጣዊ መቆራቆስ አያዋጣንም፤ አይጠቀምንም ነው የሚሉት፡፡ የሥልጣን እና የውርስ ችግሮች በእኛ ሀገር ብቻ ሳይኾን በሌሎች ዓለማትም የግጭት ምንጭ ናቸው፡፡ ውርስ ሲባል ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነትን የሚጠቀልለው ነው፤ ይሄን በሚገባ በማሥተዳደር እና ለችግሩ እልባት ያበጁ ሀገራት አድገዋል፤ እኛም መፍትሔ መቀመር አለበን ይላሉ፡፡

 

ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን የሚበጀው በታሪክ ከመጋጨት ይልቅ በታሪክ መማር፣ በትናንት ከመጣላት ይልቅ ዛሬ መሥራት፣ ችግሮችን በግጭት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በውይይት እና በምክክር መፍታት ነው ብለዋል ፕሮፌሰሩ፡፡

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰብል በወቅቱ እንዲሠበሠብ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።
Next article“ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው” አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ