ሰብል በወቅቱ እንዲሠበሠብ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።

34

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር አዋበል ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የጤፍ ሰብል ተጎብኝቷል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን ከተሸፈነው ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 191ሺህ ሄክታሩ በጤፍ ሰብል ተሸፍኗል።
በአዋበል ወረዳ በእነቢ ጭፋር ቀበሌ አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ጤፍን በኩታ ገጠም ማልማትን በስፋት እየተገበሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በኩታ ገጠም መዝራታችን ዕውቀትን እና ልምድን እንድንጋራ አስችሎናል የሰብሉ ቁመናም ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል አርሶ አደሮቹ። አርሶአደሮቹ ሰብሉ ታጭዶ እና ተወቅቶ ወደ ጎተራ እስኪገባ የምርት ብክነትን ለመቀነስ በጥንቃቄ እንደሚሠሩም ነግረውናል። ሰብልን በደቦ የመሠብሠብ የማኅበረሰቡ ልምድ ምርታቸውን በወቅቱ ለመሠብሠብ እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል።

በአዋበል ወረዳ የእነቢ ጭፋር ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበበ አሸነፍ አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እና ያለብክነት እንዲሠበሥቡ ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮንን በምርት ዘመኑ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በዞኑ 183 ቀበሌዎች ጤፍን በኩታ ገጠም እያለሙ ነው ያሉት አቶ አበበ በጤፍ ከተሸፈነው 191ሺህ ሄክታር መሬት ከ80 በመቶ በላይ የለማው በኩታ ገጠም መኾኑንም ገልጸዋል። መምሪያ ኀላፊው አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በትክክለኛው ጊዜ በመሠብሠብ ብክነትን መከላከል እና የምርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ አርሶ አደሮች በመኸር ያመረቱትን ምርት በወቅቱ እንዲሠበሥቡ አሥተዳደሩ ሕግን ከማስከበር በተጓዳኝ አርሶ አደሮች ሙያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የአዋበል ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እና አርሶ አደሮች በአዋበል ወረዳ እነቢ ጭፋር ቀበሌ በኩታ ገጠም የለማ የጤፍ ሰብልን ተመልክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዛሬ ምን አገባኝ ያለ ነገ ባለተራ ነው”
Next article“በአንድነት እንኑር፤ በፍቅር እንሻገር”