“ዛሬ ምን አገባኝ ያለ ነገ ባለተራ ነው”

29

ባሕር ዳር: ኅዳር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ይህ በጓደኛየ ላይ የደረሰ እውነተኛ ገጠመኝ ነው። ሀገር ሰላም ነው ብሎ በጥዋት ተነስቶ ወደ ሥራ እየተጓዘ ነበር። ሰዓቱ ደግሞ ከጥዋቱ 12:30 ሰዓት አካባቢ። ከቤቱ ትንሽ ራቅ እንዳለ በግራ እና በቀኙ በኩል ሦስት ጎረምሶች ከበቡት። ምን እንደፈለጉ የተገለጸለት ነገር አልነበረም።

በቅጽበት አንዱ አንገቱን ቆልምሞ ያዘው። ሌላኛው እጆቹን የፊጥኝ ጨመደደው። ሦስተኛው ደግሞ ይህን ረዳት አልባ የኾነ ጓደኛየን ደረት እንደ አርማታ በደደረ እጁ በቡጢ ደጋግሞ መታው።

ራሱን ስቶ እስኪወድቅ ድረስም ደጋገመው፤ ተዝለፍልፎ መሬት ላይ ተዘረረ። የእጅ ስልኩን እና ኪሱ ውስጥ የነበረውን ብር ይዘው ምንም ፍርሃት ሳይስተዋልባቸው ቦታውን ለቀው ሄዱ።

ጓደኛየ እንደ ነገረኝ ሦስቱ ጎረምሶች ከበው ሲደበድቡት በአካባቢው ሲያልፉ የነበሩ ሰዎች እያዩ ነበር። ልጁን ከዘራፊዎች ለማስጣል ግን ያደረጉት አንድም ነገር አልነበረም።

ሌላኛው አጋጣሚ ሰውየው ባጃጅ ይሳፈራል። ጥቂት እንደተጓዙ የባጃጁ ሞተር በድንገት ይጠፋል። ይሄኔ ሹፌሩ በሞተሩ መጥፋት የተበሳጨ መሰለ። ቀኑን ሙሉ ሁኔታው ሲያስቸግረው እንደዋለ ለተሳፋሪዎች ነገራቸው።

ልብ ልትሉት የሚገባው ግን በዳር በኩል የተቀመጠው የዘረፋው ወጥመድ ውስጥ የገባው ብቻ እንጅ ቀሪዎች ሁለቱ “ተሳፋሪዎች” ሳይኾኑ የዝርፊያው ግብረ አበሮች ናቸው።

እናም ይህንን ምኑም ያልተገለጠለት በዳር በኩል የነበረ ተሳፋሪ “እባክህ ውረድ እና ትንሽ ግፋልኝ፤ ስትገፋ ሞተሯ ይነሳል” አሉት። ሰውየውም እንደተባለው ሻንጣውን ከባጃጇ ውስጥ ትቶ ሊገፋ ወረደ። ለዘረፋ ታጭቶ የነበረው ሰው ወጥመዱ አልተገለጠለትም።

እንደወረደ “ጠፋ” የተባለው ሞተር ይንደቀደቅ ጀመረ። ባጃጇ ሊገፋት የወረደውን ሰው ከኋላ ትታ ወደ ፊት ከነፈች። ይሄኔ ሰውየው እየተዘረፈ እንደኾነ ተገለጠለት እና “ሌባ! ሌባ! ሌባ” እያለ የድረሱልኝ ጩኸቱን አሰማ።

ዘራፊዎችም በፍጥነት ማምለጣቸውን ቀጠሉ፤ ሰውየውም አካባቢው የነበረውን በርካታ ሕዝብ “እባካችሁ ዘረፉኝ ያዙልኝ፤ የሰው ያለኽ” እያለ ባጃጇን ተከትሎ ይሮጣል። ማንም ግን ዘራፊዎችን ሊያስቆምለት አልፈለገም።

ይህ የዘረፋ ሙከራ ደግሞ ለየት ያለ መልክ አለው። ዘራፊው ሽጉጥ ተጠቅሞ ነው ዘረፋውን የፈጸሙው። ተዘራፊው ዘራፊውን እየጠቆመ “ያዙልኝ” እያለ ጩኸቱን ያቀልጠዋል። ዘራፊው ደግሞ ሽጉጡን በቀኝ እጁ ከፍ አድርጎ ለሕዝቡ እያሳየ ሩጫውን ተያይዞታል። ሰዎችም ቶሎ ብለው መንገድ ይለቁለታል።

ከተዘራፊው ጎን ሆኖ ሌባውን ለመያዝ ወይም የማስቆም ሙከራ ያደረገ ግን አይታይም ነበር። ይኹን እንጅ ይህ ክስተት መጨረሻው የተበዳይን እንባ ያበሰ ኾኖ ተቋጭቷል። የመከላከያ ሠራዊት አባል በድንገት ከተፍ አለ፤ ዘራፊውም ተያዘ። ሁሉም በደስታ ፈነደቀ።

እነዚህ ሦስቱም የዝርፊያ ድርጊቶች የሚጋሩት አንድ መልክ አለ። ይኸውም ዘረፋው ሲፈጸም ተዘራፊዎች እርዱን ሲሉ ዘራፊዎችን ለመያዝ ፍላጎት ያለው ሰው ቁጥሩ አነስተኛ ነው።

አሳሳቢው ነገር ያለውም እዚህ ጋ ነው። እንዴት ዘረፋ ላያስደነግጠን ቻለ? ፍርሐት ወይስ ምን አገባኝነት? ወይስ በሕግ እና በሥርዓት ተስፋ መቁረጥ? መልሱን በትክክል መመለስ የሚችል ያለ አይመስለኝም።

ሁላችንም በጋራ የሚያስማማን ግን የአንዱ ችግር የሌላችንም መኾኑን መገንዘብ ላይ ችላ ብለናል። ሰው ለሰው መድሐኒቱ የሚባለውን ሃቅ ብናውቅም ቅሉ ተግባሩ ላይ ግን ወድቀን ተገኝተናል።

ዋጋ ሳይከፈል ሰውን መርዳት መቼም አይቻልም።ለሰው ችግር ስንደርስ የአካልጉዳት ልናስተናግድ እንችል ይኾናል። ካለን ላይ ቀንሰን ገንዘብ ልንከፍል እንችልም ይኾናል።

ግን የምንከፍለው ዋጋ ለሁላችንም የነገ ሰላማዊ ኑሯችን እንዲቀጥል ዋስትና የሚኾን እና የተበደሉ ወገኖቻችን እንባቸውን የሚያብስ፤ ወደ ቀደመ ደስታቸውም የሚመልስ የተቀደሰ ተግባር ነው።

መሰለ የዝርፊያ ተግባራት ከተመልካቹ የሚጎድለው ሌባውን ለመያዝ የመጀመሪያዋን ተነሳሽነት የሚያሳይ ሰው መጥፋቱ ነበር። የተፈጸመው ድርጊት ዘረፋ ነው። ዘረፋ ደግሞ እንደ መጣንበት የታሪክ ልምምድም እንደየ እምነቶቻችን ቀኖናም እጅግ የተወገዘ ጽዩፍ መኾኑ ሁላችንም የሚያስማማ ነው።

በዚህ ከተስማማን ደግሞ ዝርፊያ ተግባር ላይ የተሠማራ ሰው ሲያጋጥመን ሁላችንም በድርጊቱ አሳፋሪነት መስማማታችን አይቀሬ ነው። መልስ የማናገኝለት ጉዳይ ግን ሰው ተዘርፎ እርዱኝ እያለ ስንመለከት ሁላችንም በአንድነት ተረባርበን ሌባን ለመያዝ ችላ ማለታችን ምስጢሩ ምንድን ነው የሚለው ነው።

ምን አገባኘነት የሚያዋጣ መፍትሔ ነው ብለን አስበን ይሆን? ከኾነም ዛሬ ምን አገባኘ ያልነው ነገ ከነገ ወዲያ የራሳችን ጉዳየ ኾኖ እንደሚመጣ እንመለከታለን።

ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው። ማለትም እዚች ፕላኔት ላይ ህልውናውን አስጠብቆ ለመቆየት ከአምሳያው ጋር በኅብረት መቆም ግድ ይለዋል። የሰው ልጅ አሁን ካለበት የሥልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሰውም በዘመን ጉዞው ላይ የገጠሙትን ፈተናዎች ተጋፍጦ መፍትሔ በማበጀቱ መኾኑን እናውቃለን።

ወረርሽኝ፣ ጦርነት፣ የባርያ ንግድ፣ የቅኝ ግዛት ቀንበር፣ ረሃብ የመሳሰሉትን አስከፊ ችግሮች በትብብር ባይጋፈጣቸው ኖሮ ዛሬ ከተደረሰበት ደረጃ ላይ ይገኝ ነበርን?

እንኳንስ ከአምሳያው የሰው ልጅ ጋር ከሌሎች ፍጥረታት ጋርም በትብብር እና በስምምነት ካልኖረ ሕልውናው ስጋት ላይ ይወድቃል፡፡ ለምሳሌ የምንተነፍሰውን ኦክስጅን የምናገኘው ከዛፎች ነው። ይህ የሚያሳየው የሰው ልጅ ብቻውን ለመቆም ወይም ተነጣጥሎ ለመጓዝ አይቻለውም ማለት ነው። እናም ኅብረት እና ትብብር ግድ ይለናል።

እገሌ የተባለ ሰው ተዘረፈ ማለት እኔ ተዘረፍኩ ማለት ነው። ዛሬ እገሊት ስትዘረፍ በዝምታ ወይም በምን አገባኝነት አለፍኳት ማለት ነገ እኔን ለዘራፊዎች አመቻቸሁ ማለት ነው። ወይም የምዘረፍበትን እድል አሰፋሁት ማለት ነው።

ምክንያቱም ሌቦች የሚያዙበትን እና ተጠያቂ የሚኾኑበትን ሥራ አልሠራሁም እና። ወንጀሉ የሚያቆምበትን ድርጊት አልፈጠምኩምና ነው።

የሆነ ቦታ ላይ የተከሰተን ወንጀል በኅብረት ካወገዝነው እና ከተከላከልነው ያንን ተመሳሳይ ወንጀል ድጋሚ የምንመለከትበት እድልም አይኖርም። በምን አገባኝነት ካለፍነው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠኑ እና አይነቱ እየጨመረ በየቀኑ ያጋጥመናል።

ከዚያም ከእለታት አንድ ቀን ሌሎች ላይ የተመለከትነውም ኾነ የሰማነው ጉዳይ እኛ ላይ ደርሶ የችግሩ ሰለባ መኾናችን አይቀሬ ነው ባይ ነኝ።

እንዴት ከተባለ በጎች መሃል የገባ ተኩላ እንዴት የተወሰኑ በጎችን ብቻ ነክሶ ሊቆም ይችላል? በጋራ ኾነው የሚድኑበትን መፍትሔ ካልዘየዱ በስተቀር ወይም እረኛቸው ደርሶ ካልታደጋቸው በስተቀር።

ሌላ ሰው ላይ የደረሰ ችግር በምን አገባኝነት ችላ ካልነው ውሎ አድሮ በራሳችን ላይ መድረሱ የማይቀር ነገር ነው።

ዘረፋን ለመከላከል ትብብር ይጎድለናል ስል ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር የሁላችንም በጋራ መቆም ይጠይቃል እያልኩ ነው። ሰዎችን የሚተባበሩ መልካም ሰዎች የሉም እያልኩ እንዳልሆነ እንድትረዱልኝ አሳስባለሁ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ በሌላው ላይ የደረሰው ችግር የኔም ነው የሚለው የአንድነት እሴታችን እየተሸረሸረ ነው ለማለት እንጅ።
አሁን አሁን በየአካባቢው ዘራፊዎች በዝተው እየተመለከትን ነው።

እንደኔ ሐሳብ ለዚህ ምክንያቱ አለመተባበራችን ነው። ገጣሚውም ”እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሃረግ፣ እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደበግ”። ያለው ምን አገባኝነት ምን ያህል ለከፋ ችግር እንደሚዳርግ ለማሳየት ነውና ዝርፊያን እና ሕገ ወጥነትን ለመከላከል አንዳችን የሌላችን ዘብ እንሁን እላለሁ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሌማት ትሩፋት የአርሶ አደሮችን ሕይዎት ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ መኾኑን በኦሮሚያ ክልል የባሌ ዞን አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleሰብል በወቅቱ እንዲሠበሠብ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።