ሌማት ትሩፋት የአርሶ አደሮችን ሕይዎት ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ መኾኑን በኦሮሚያ ክልል የባሌ ዞን አሥተዳደር አስታወቀ።

56

አዲስ አበባ:ኅዳር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መሪዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጎባ ወረዳ በሌማት ቱሩፋት እየተተገበሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል። በባሌ ዞን የጎባ ወረዳ አርሶ አደር አበራ ኩራ ከመደበኛው የእርሻ ሥራ ባሻገር በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ሕይዎታቸውን እየመሩ መኾኑን አንስተዋል።

ከ86 በላይ ዘመናዊ እና ባሕላዊ የንብ ቀፎዎች እንዳላቸውም ለአሚኮ ተናግረዋል። ከእነዚህ ቀፎዎችም በዓመት ከ100 ኪሎ ግራም በላይ የማር ምርት እንደሚጠብቁ ነው የገለጹት። በዓመት ሦሥት ጊዜ ማር እንደሚቆርጡ እና ከአንድ ዘመናዊ ቀፎ ብቻ እስከ 7 ኪሎ ግራም የማር ምርት እንደሚያገኙ አንስተዋል።

አሁን ላይ አንድ ኪሎ ማር እሰከ 1 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ከንብ ማነብ ሥራ በተጨማሪ በመኖሪያ ግቢያቸው ዶሮ በማርባት እና እንሰሳትን በማድለብ ተግባር መሠማራታቸውንም አንስተዋል። በሌማት ቱሩፋት የተሠማሩ ሌላኛዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ብርቄ ተካ ከአሁን በፊት በአስቸጋሪ የኑሮ ደረጃ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡

ወይዘሮ ብርቄ አሁን ላይ ባላቸው ትንሽ ግቢ የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን በማልማት ሕይዎታቸውን እየመሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ገቢ የሚያስገኙ የተለያዩ አትክልቶችን ከማልማት በተጨማሪ በ50 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች የንብ ማነብ ሥራ መጀመራቸውንም ነው የገለጹት። የባሌ ዞን አሥተዳዳሪ አብዱላኪም አልዩ ባሌ ዞን በሰላም፣ በልማት እና በቱሪዝም የታደለች እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት መኾኗን አንስተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት እንደ ሀገር የተጀመረው ራስን በምግብ የመቻል ዕቅድን ከግብ ለማድረስ ከመደበኛው የእርሻ ተግባር ባሻገር በዞኑ የሌማት ቱሩፋትን ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል። በሌማት ትሩፋት የዞኑን አርሶ አደሮች ሕይዎት ለማሻሻል በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።

አቶ አብዱላኪም በበጀት ዓመቱ 110 ሺህ ዝርያቸው የተሻሻሉ ከብቶችን ለማዳቀል ታቅዶ እየተሠራ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት። እሰካሁንም 57 ሺህ በላይ ዝርያቸው የተሻሻሉ ከብቶችን ማዳቀል ተችሏል ነው ያሉት። ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ተፋሰሶች ወጣቶችን በንብ ማነብ ሥራ በማደራጀት ማርን በብዛት እና በጥራት እንዲያመርቱ በትኩረት እየተሠራ ነው።

በበጀት ዓመቱ 82 ሺህ 500 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ሲኾን እስካሁን ከ22 ሺህ 600 በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረግም ተችሏል።

ዘጋቢ፡- ቲዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ከሩዝ ሰብል 14 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሠራ ነው።
Next article“ዛሬ ምን አገባኝ ያለ ነገ ባለተራ ነው”