
ደብረ ታቦር: ኅዳር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) አማራ ክልል ለሩዝ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል። ባለፉት ዓመታት ሩዝ በደቡብ ጎንደር ዞን በተለይም በፎገራ ወረዳ ላይ ብቻ ይመረት እንደነበር አስታውሰዋል። በ2015/16 የምርት ዘመን ከ80 ሄክታር የማይበልጥ መሬት ብቻ በሩዝ ተሸፍኖ እንደነበርም ገልጸዋል።
በ2016/17 የምርት ዘመን ግን ሩዝን በፎገራ ብቻ ሳይኾን በሌሎችም የክልሉ 12 ዞኖች ማልማት ተችሏል። በምርት ዘመኑ በክልሉ 150 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ተሸፍኗል። በተደረገው የሰብል ቁመና ግምገማ መሰረትም 14 ሚሊየን ኩንታል የሩዝ ምርት ይገኛል ነው ያሉት ዶክተር ድረስ።
በዛሬው ዕለት የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ምልከታ ያካሄዱበት የፎገራ አካባቢ ለሩዝ ምርት ከፍተኛ አቅም ያለው ነው። ዶክተር ድረስ እንደገለጹት በወረታ እና አካባቢው በአንድ ሄክታር በአማካኝ 60 ኩንታል የሩዝ ምርት ይገኛል። የተለየ እንክብካቤ ያደረጉ እና ግብዓት በበቂ ኹኔታ የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ከአንድ ሄክታር መሬት እስከ 110 ኩንታል የሩዝ ምርት እንዳገኙም ተናግረዋል።
ዶክተር ድረስ በተያዘው የምርት ዘመን የሰብሉ ቁመና በተሻለ ደረጃ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ይህ ሊኾን የቻለውም የግብዓት አቅርቦት ሥራው በትኩረት በመከናወኑ ነው ብለዋል። በክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር በጽናት በመቋቋም አርሶ አደሮች ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በወቅቱ እንዲያገኙ ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል።
ከመጀመሪያ እርሻ ጀምሮ እስከ ዘር እና መንከባከብ ድረስ የግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደሮችን ይደግፉ እንደነበርም ዶክተር ድረስ ተናግረዋል። ይህም በሩዝ እና በሌሎችም የሰብል አይነቶች የታለመውን የምርት መጠን ለማግኘት የሚያስችል ነው ብለዋል። በአማራ ክልል ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ከእርሻ ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ለአርሶ አደሮች ድጋፍና ክትትል ይደረጋል፤ የማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ስርጭትም በወቅቱ እንዲደርስ ይሠራል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።
“በ2016/17 የምርት ዘመን በክልሉ 7 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተሰራጭቷል፤ ይህም አኹን ለምናየው የሰብል ቁመና እና ምርት አብቅቶናል” ነው ያሉት ዶክተር ድረስ። በቀጣይም አርሶ አደሮች ከዚህ የተሻለ የምርት መጠን እና ጥራት እንዲያስመዘግቡ የሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን እና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ለማቅረብ ግብርና ቢሮው አበክሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ በዞኑ 19 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል አጠቃላይ የሰብል ምርት ይሰበሰባል ብለዋል። ፎገራ ወረዳ በተለይም በሩዝ ምርት እንደ ሀገርም ትልቅ አቅም ያለው መኾኑን አንስተዋል። በተያዘው የምርት ዘመን በፎገራ ወረዳ ብቻ 72 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል ተሸፍኗል። ከዚህም 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ብለዋል የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ።
አቶ ጥላሁን እንዳሉት የዞኑ ሕዝብ ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ፣ ለሥራ ያለው ክብር እና በጋራ የመሥራት እሴቱ ለምርት እና ምርታማነት አብቅቶታል። አሚኦ ዲጂታል ሚዲያ ካነጋገራቸው የወረዳው አርሶ አደሮች መካከል የሻጋ ቀበሌ ነዋሪው ዋለልኝ አስራደ ሩዝ የኑሯችን መሠረት ነው ብለዋል።
በ2016/17 የምርት ዘመን በቂ የማዳበሪያ ግባት እንዳገኙ እና ይህም በዓመቱ ከ 10 ኩንታል በላይ ሩዝ ለማምረት እንደሚያበቃቸው ገልጸዋል።
ሌላው የፎገራ ወረዳ ሰይፍ አጥራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አዛናው ዓለሙ በሩዝ ምርት ላይ ተግተው እየሠሩ መኾኑን ነግረውናል።
ትራክተር እና የሰብል መሰብሰቢያ ማሽን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሮች እንዲቀርብም ጠይቀዋል። የዚህ ዓመት የማዳበሪያ ስርጭት አልባሌ ስርቆትን ያስቀረ እንደነበር እና መንግሥትንም የሚያስመሠግን ተግባር መኾኑን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!