
ደብረ ታቦር: ኅዳር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ወረታ ከተማ ተገኝተው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የግንባታ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ ኀላፊ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና ሌሎችም የዞን እና የክልል ከፍተኛ መሪዎች በምልከታው ላይ ተገኝተዋል።
ከፍተኛ መሪዎቹ ከተመለከቷቸው ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ፣ የዱቄት እና የምግብ ነክ ፋብሪካዎች ይገኙበታል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የክልሉ ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በወረታ ከተማ እና አካባቢው በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ትልቅ የአዋጭነት አቅም እንዳለ ተናግረዋል።
በተለይም በሰብል ልማት እምቅ ጸጋ በመኖሩ በምግብ ነክ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሚሰማሩ አልሚዎች ምቹ መኾኑን ጠቅሰዋል። ዶክተር አሕመዲን በወረታ ከተማ ውስጥ ጥሩ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ጅምር መኖሩንም ተናግረዋል። በከተማው ውስጥ የተገነቡ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው በማምረት ለሀገርም ጭምር የኢኮኖሚ ግብዓት እንዲኾን የክልሉ ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ነው ያሉት። በቂ የኀይል አቅርቦት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ትኩረት ሰጥተን እንሠራለንም ብለዋል።
ከፍተኛ የክልል መሪዎችን ተቀብለው የልማት ሥራዎችን ያስጎበኙት የወረታ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት ፈረደ በከተማዋ 13 ባለሃብቶች ፋብሪካዎችን ገንብተው ወደምርት ለመግባት እየተጠባበቁ ነው ብለዋል። በቂ የኀይል አቅርቦት እና መሠረተ ልማት እንደተሟላ በቀጥታ ወደ ምርት እንደሚገቡም ተናግረዋል።
በግንባታ ላይ ከተሠማሩ ባለሃብቶች በተጨማሪ 41 ባለሃብቶች የልማት ዕቅዳቸውን አቅርበው መሬት መጠየቃቸውንም ተናግረዋል። ለዚህም ከሦስተኛ ወገን የጸዳ በቂ የመሬት አቅርቦት ተዘጋጅቷል ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!