ጎንደር ለጥምቀት በዓል ከ1 ሚሊዮን በላይ እንግዶችን ትቀበላለች።

43

ጎንደር: ኅዳር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዘንድሮው ዓመት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ከ1 ሚሊዮን በላይ እንግዶችን ለመቀበል እየተዘጋጀ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገልጿል፡

የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በዘንድሮው ዓመት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ከ1 ሚሊዮን በላይ እንግዶችን ለመቀበል ዐቢይ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተደራጅተው ሥራዎችን እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በጎንደር እና በአካባቢው ከሚገኙ የመስብ ሃብቶች ባሻገር ከማይጨበጡ ቅርሶች መካከል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ መኾኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ ከከተማዋ ወጣቶች እና ከኅብረተሰቡ ጋር ምክክር እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በዓሉን በድምቀት ለማክበርም ከዋናው የጥምቀት በዓል ባሻገር ከጥር 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ13 ቀናት ልዩ ልዩ ኩነቶች እንደሚፈጠሩም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ ዲያስፖራዎች በሀገራቸው ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትውፊቶች እንዲሳተፉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በዕለቱ የጥምቀት ዐቢይ ኮሚቴ አባላት በመከናወን ላይ የሚገኙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ገምግሟል፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ ባሕል ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ልዕልና አበበ እንደገለጹት የባህረ ጥምቀት የጥገና እና የማስዋብ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ቀጣይ ከሁሉም የጥምቀት በዓል ንዑሳን ከሚቴዎች ጋር በቅርበት የሚሠራ ሲኾን የሕዝብ የውይይት መድረኮችም በየደረጃው እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአቋራጭ ተማሪዎችን ቁጥር የቀነሰው የተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር።
Next article“ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)