
ባሕር ዳር: ኅዳር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ በተመረጡ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር እየተሰጠ መኮኑን የከተማ አሥተዳደሩ አስታውቋል። ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገች የቁልቋል ሜዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ቤተሰቦቿ የቀን ሥራ ሠርተው አራት ልጆችን ከእጅ ወደ አፍ የኾነ ሕይዎትን ይመራሉ።
የኑሮ ወድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ እና መቋቋም ባለመቻላቸው የባለ ታሪካችን ወላጆች የእሷን የወደፊት ሕይዎት የሚያጨልም ውሳኔ አሳረፉ። “አንቺ ሴት በመኾንሽ በቅርብ ዓመታት ባል ሊመጣልሽ ይችላል፤ እስከዚያው ድረስ ትምህርቱን አቋርጭና ከሰው ቤት ሥሪ፤ እኛንም በገቢ ደጉሚ”የሚል ነበር።
በወላጆቿ ውሳኔ የተጨነቀችው ተማሪ በዚህ ኹኔታ እያለች የምገባ መርሐ ግብሩ በትምህርት ቤቱ መጀመሩ የሷን እና የመሰል ጓደኞቿን ሕይወት የታደገ እንደኾ ተናግራለች። ባለ ታሪካችን ብቻ ሳትኾን ትንሽ ወንድሟ እና በርካታ ትምህርት ለማቋረጥ በቋፍ ላይ የነበሩ ታዳጊዎችም የዕድሉ ተጠቃሚ ኾኑ።
“ጠንክሬ በመማር ዛሬ ላይ እየረዳኝ ያለውን ወገኔን ሳይንቲስት በመኾን ለመርዳት ሕልም አለኝ፤ ወንድሜም በደስታ በትምህርቱ ተግቶ እየተማረ ነው” ብላለች ታዳጊዋ።
በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የየካቲት 23 አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት የርባለም መለሰ “በትምህርት ቤታችን በርካታ በዝቅተኛ ሕይወት የሚኖሩ ቤተሰቦች ያሏቸው ልጆች እየተማሩ ይገኛሉ፤ ነገር ግን ልጆቹ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በሄድ መለስ ነው። መንግሥት የተማሪዎች ምገባን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች 4 ሺህ ለሚጠጉ ተማሪዎች ምገባ መጀመሩን ተናግረዋል። ይህም የአቋራጭ ተማሪዎችን ቁጥር በእጅጉ ይቀንሰዋል ብለዋል። ወደፊት በጥናት ላይ በመመርኮዙም ተመክሮውን ለማስፋት ይሠራል ነው ያሉት።
“የምገባ ፕሮግራም አቋራጭ ተማሪዎችን ከመቀነስ ባለፈ ነገ ላይ ለወገን እና ሀገር የሚጠቅሙ ጎበዝ ተማሪዎችን ማፍራት ያስችላል” ብለዋል አቶ ጎሹ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!